17 ኢየሱስም የሚናገሩትን ሰምቶ፣ “ሐኪም የሚያስፈልጋቸው ሕመምተኞች እንጂ ጤነኞች አይደሉም፤ እኔ ኀጢአተኞችን እንጂ ጻድቃንን ወደ ንስሓ ልጠራ አልመጣሁም” አላቸው።
18 የዮሐንስ ደቀ መዛሙርትና ፈሪሳውያን ይጾሙ ነበር፤ አንዳንድ ሰዎችም መጥተው ኢየሱስን፣ “የዮሐንስና የፈሪሳውያን ደቀ መዛሙርት ሲጾሙ፣ የአንተ ደቀ መዛሙርት የማይጾሙት ለምንድን ነው?” አሉት።
19 ኢየሱስም፣ እንዲህ አላቸው፤ “ሙሽራው ከእነርሱ ጋር እያለ ሚዜዎቹ ሊጾሙ ይችላሉን? ሙሽራው ከእነርሱ ጋር እያለ ሊጾሙ አይችሉም፤
20 ሙሽራው ከእነርሱ የሚወሰድበት ወቅት ይመጣል፤ በዚያን ጊዜ ግን ይጾማሉ።
21 “በአሮጌ ልብስ ላይ አዲስ ጨርቅ የሚጥፍ ማንም የለም፤ ይህ ቢደረግ ግን፣ አዲሱ ጨርቅ አሮጌውን ይቦጭቀዋል፤ ቀዳዳውም የባሰ ይሰፋል።
22 እንዲሁም አዲስ የወይን ጠጅ በአሮጌ አቍማዳ የሚያስቀምጥ የለም፤ ይህ ከተደረገማ የወይን ጠጁ አቍማዳውን ያፈነዳዋል፤ የወይን ጠጁም አቍማዳውም ይበላሻሉ። ስለዚህ አዲስ የወይን ጠጅ መቀመጥ ያለበት በአዲስ አቍማዳ ነው።”
23 በሰንበት ቀን ኢየሱስ በእርሻ መካከል ሲያልፍ፣ አብረውት በመጓዝ ላይ የነበሩት ደቀ መዛሙርቱ እሸት ይቀጥፉ ጀመር።