ራእይ 5:6-12 NASV

6 ከዚያም በዙፋኑና በአራቱ ሕያዋን ፍጡራን፣ በሽማግሌዎቹም መካከል የታረደ የሚመስል በግ ቆሞ አየሁ፤ በጉም ሰባት ቀንዶችና ሰባት ዐይኖች ነበሩት፤ እነርሱም ወደ ምድር ሁሉ የተላኩት ሰባቱ የእግዚአብሔር መናፍስት ናቸው።

7 እርሱም መጥቶ በዙፋኑ ላይ ከተቀመጠው ቀኝ እጅ መጽሐፉን ወሰደ።

8 መጽሐፉን በወሰደ ጊዜ አራቱ ሕያዋን ፍጡራን፣ ሃያ አራቱ ሽማግሌዎችም በበጉ ፊት በግምባራቸው ተደፉ፤ እያንዳንዳቸውም የቅዱሳን ጸሎት የሆኑትን በገናና ዕጣን የሞላበትን የወርቅ ሙዳይ ይዘው ነበር።

9 እንዲህም እያሉ አዲስ መዝሙር ዘመሩ፤“መጽሐፉን ልትወስድ፣ማኅተሞቹንም ልትፈታ ይገባሃል፤ምክንያቱም ታርደሃል፤በደምህም ከነገድ ሁሉ፣ ከቋንቋ ሁሉ፣ከወገን ሁሉ፣ ከሕዝብ ሁሉ ሰዎችን ለእግዚአብሔር ዋጅተሃል።

10 ለአምላካችንም መንግሥትና ካህናት አድርገሃቸዋል፤እነርሱም በምድር ላይ ይነግሣሉ።”

11 ከዚያም ተመለከትሁ፤ የብዙ መላእክትን ድምፅ ሰማሁ፤ ቍጥራቸውም ሺህ ጊዜ ሺህና እልፍ ጊዜ እልፍ ነበረ፤ እነርሱም በዙፋኑና በሕያዋን ፍጡራኑ፣ በሽማግሌዎቹም ዙሪያ ከበው ነበር፤

12 በታላቅ ድምፅም እንዲህ ብለው ዘመሩ፤“የታረደው በግ ኀይልና ባለጠግነት፣ጥበብና ብርታት፣ክብርና ሞገስ፣ ምስጋናም፣ሊቀበል ይገባዋል።