1 ዜና መዋዕል 29:17-23 NASV

17 አምላኬ ሆይ፤ ልብን እንደምትመረምርና ቅንነትን እንደምትወድ ዐውቃለሁ፤ እኔም ይህን ሁሉ የሰጠሁት በበጎ ፈቃድና በቀና መንፈስ ነው። አሁንም በዚህ ያለው ሕዝብህ በበጎ ፈቃዱ እንዴት እንደ ሰጠ አይቻለሁ።

18 የአባቶቻችን የአብርሃም፣ የይስሐቅ፣ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ሆይ፤ ይህን ዐሳብ ለዘላለም በሕዝብህ ልብ ጠብቀው፤ ልባቸውንም ለአንተ ታማኝ አድርገው።

19 ትእዛዞችህን፣ ደንብህንና ሥርዐትህን እንዲጠብቅ፣ እኔ ባዘጋጀሁለት ነገሮች ታላቅ ሕንጻ ለመሥራት እንዲችል፣ ለልጄ ለሰሎሞን ፍጹም ፈቃደኝነት ስጠው።

20 ከዚያም ዳዊት ለመላው ጉባኤ፣ “አምላካችሁን እግዚአብሔርን ወድሱት” አላቸው። ስለዚህ የአባቶቻቸውን አምላክ እግዚአብሔርን ወደሱ፤ በእግዚአብሔር በንጉሡም ፊት ተደፍተው ሰገዱ።

21 በማግስቱም ለእግዚአብሔር መሥዋዕት ሠዉ፤ የሚቃጠል መሥዋዕትም አቀረቡ፤ ይህም አንድ ሺህ ወይፈን፣ አንድ ሺህ አውራ በግ፣ አንድ ሺህ የበግ ጠቦት ሲሆን፣ ከመጠጥ ቊርባኖቻቸውና ከሌሎች መሥዋዕቶች ጋር ስለ እስራኤል ሁሉ በብዛት አቀረቡ።

22 በዚያችም ዕለት በእግዚአብሔር ፊት በታላቅ ደስታ በሉ፤ ጠጡም።ከዚያም የዳዊት ልጅ ሰሎሞን ንጉሥ መሆኑን ለሁለተኛ ጊዜ በይፋ ዐወቁ፤ ገዥ እንዲሆንም በእግዚአብሔር ፊት ቀቡት፤ ሳዶቅንም ካህናቸው እንዲሆን ቀቡት።

23 ሰሎሞንም ነግሦ በአባቱ በዳዊት ምትክ በእግዚአብሔር ዙፋን ላይ ተቀመጠ፤ ተከናወነለት፤ እስራኤልም ሁሉ ታዘዙለት።