1 አክዓብ ከሞተ በኋላ ሞዓብ በእስራኤል ላይ ዐመፀ።
2 በዚህ ጊዜ አካዝያስ በሰማርያ ካለው እልፍኝ ሰገነቱ ላይ ሳለ፣ ከዐይነ ርግቡ ሾልኮ ወድቆ ነበርና ታመመ፤ ስለዚህ፣ “ሄዳችሁ ከዚህ ሕመም እድን እንደሆነ የአቃሮንን አምላክ ብዔልዜቡልን ጠይቁ” ሲል መልእክተኞች ላከ።
3 የእግዚአብሔር መልአክ ግን ቴስብያዊውን ኤልያስን እንዲህ አለው፤ “ተነሥተህ የሰማርያን ንጉሥ መልእክተኞች ለመገናኘት ውጣና፣ ‘የአቃሮንን አምላክ ብዔልዜቡልን ለመጠየቅ የምትሄዱ በእስራኤል አምላክ ስለሌለ ነውን?’ ብለህ ጠይቃቸው።
4 ስለዚህ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘ከተኛህበት ዐልጋ አትነሣም፤ በርግጥ ትሞታለህ።’ ” ከዚያም ኤልያስ ሄደ።