1 በዚህ ጊዜ አክዓብ በሰማርያ ሰባ ወንዶች ልጆች ነበሩት፤ ስለዚህ ኢዩ ደብዳቤ ጽፎ ለኢይዝራኤል ሹማምንት፣ ለሽማግሌዎችና የአክዓብን ልጆች ለሚያሳድጉ ሞግዚቶች ወደ ሰማርያ ላከ፤ መልእክቱም እንዲህ የሚል ነበር፤
2 “የጌታችሁ ልጆች ከእናንተ ጋር ስለሆኑ፣ ሠረገሎችና ፈረሶች፣ የተመሸገች ከተማና መሣሪያም ስላላችሁ፣ ይህ ደብዳቤ እንደ ደረሳችሁ ወዲያውኑ
3 ከጌታችሁ ልጆች መካከል ብልጫ ያለውንና ተገቢ ነው የምትሉትን መርጣችሁ በአባቱ ዙፋን አስቀምጡት። ከዚያም ስለ ጌታችሁ ቤት ተዋጉ።”
4 እነርሱ ግን እጅግ ፈርተው ነበርና፣ “ሁለት ነገሥታት ሊቋቋሙት ያልቻሉትን ሰው እኛ እንዴት ልንቋቋመው እንችላለን?” አሉ።
5 ስለዚህ የቤተ መንግሥቱ አዛዥ፣ የከተማዪቱ ገዥ፣ ሽማግሌዎችና የልጆቹ ሞግዚቶች፣ “እኛ ያንተው አገልጋዮች ነን፤ ትእዛዝህን ሁሉ እንፈጽማለን፤ እኛ ማንንም አናነግሥም፤ ደስ የሚያሰኝህን ሁሉ አንተው አድርግ” በማለት ይህን መልእክት ለኢዩ ላኩ።