11 ስለዚህ ኢዩ ከአክዓብ ቤት የቀረውን ሁሉ፣ ታላላቆቹን ሰዎች በሙሉ፣ የቅርብ ወዳጆቹንና ካህናቱን አንድም ሳይቀር በኢይዝራኤል ገደላቸው።
12 ከዚያም ኢዩ ተነሥቶ ወደ ሰማርያ ሄደ፤ ቤትኤከድ ወደተባለው የበግ ጠባቂዎችም ቤት ሲደርስ፣
13 ከይሁዳ ንጉሥ ከአካዝያስ ሥጋ ዘመዶች ጥቂቶቹን አግኝቶ፣ “እናንተ እነማን ናችሁ?” ሲል ጠየቃቸው፤እነርሱም፣ “እኛ የአካዝያስ ሥጋ ዘመዶች ነን፤ ንጉሣዊውን ቤተ ሰብና የእቴጌይቱን ልጆች ለመጠየቅ ወደዚህ ወርደን መጥተናል” አሉ።
14 እርሱም፣ “ከነሕይወታቸው ያዟቸው!” ሲል አዘዘ፤ ስለዚህ ከነሕይወታቸው ወስደው በቤት ኤከድ ጒድጓድ አጠገብ አርባ ሁለቱን ሰዎች ገደሏቸው፤ አንድ እንኳ አላስቀረም።
15 ከዚያም ተነሥቶ ሲሄድ የሬካብ ልጅ ኢዮናዳብ ወደ እርሱ ሲመጣ መንገድ ላይ አገኘው። ኢዩም ሰላምታ ሰጥቶት “ልቤ ለልብህ ታማኝ የሆነውን ያህል ያንተስ ልብ ለልቤ እንዲሁ ታማኝ ነውን?” ሲል ጠየቀው።ኢዮናዳብም፣ “አዎን፤ ነው!” ብሎ መለሰ።ኢዩም፣ “እንግዲያውስ እጅህን ስጠኝ” አለው። እጁንም ሰጠው፤ ከዚያም ኢዩ ደግፎ ወደ ሠረገላው አወጣው።
16 ኢዩም፣ “በል አብረን እንሂድና ለእግዚአብሔር ያለኝን ቅናት እይልኝ” አለው፤ ከዚያም በሠረገላው ይዞት ሄደ።
17 ኢዩ ወደ ሰማርያ በደረሰ ጊዜ፣ ከአክዓብ ቤተ ሰብ በዚያ የቀረውን ሁሉ ገደለ። ለነቢዩ ለኤልያስ በተነገረውም የእግዚአብሔር ቃል መሠረት አጠፋቸው።