2 “የጌታችሁ ልጆች ከእናንተ ጋር ስለሆኑ፣ ሠረገሎችና ፈረሶች፣ የተመሸገች ከተማና መሣሪያም ስላላችሁ፣ ይህ ደብዳቤ እንደ ደረሳችሁ ወዲያውኑ
3 ከጌታችሁ ልጆች መካከል ብልጫ ያለውንና ተገቢ ነው የምትሉትን መርጣችሁ በአባቱ ዙፋን አስቀምጡት። ከዚያም ስለ ጌታችሁ ቤት ተዋጉ።”
4 እነርሱ ግን እጅግ ፈርተው ነበርና፣ “ሁለት ነገሥታት ሊቋቋሙት ያልቻሉትን ሰው እኛ እንዴት ልንቋቋመው እንችላለን?” አሉ።
5 ስለዚህ የቤተ መንግሥቱ አዛዥ፣ የከተማዪቱ ገዥ፣ ሽማግሌዎችና የልጆቹ ሞግዚቶች፣ “እኛ ያንተው አገልጋዮች ነን፤ ትእዛዝህን ሁሉ እንፈጽማለን፤ እኛ ማንንም አናነግሥም፤ ደስ የሚያሰኝህን ሁሉ አንተው አድርግ” በማለት ይህን መልእክት ለኢዩ ላኩ።
6 ከዚያም ኢዩ፣ “እንግዲህ የእኔ ወገን ከሆናችሁና ከታዘዛችሁኝ የጌታችሁን ልጆች ራስ ቈርጣችሁ ነገ በዚህ ሰዓት ይዛችሁልኝ ወደ ኢይዝራኤል እንድትመጡ” ሲል ደግሞ ጻፈላቸው።በዚህም ጊዜ ሰባው የንጉሡ ልጆች በከተማዪቱ ውስጥ ታዋቂ በሆኑ አሳዳጊዎቻቸው ዘንድ ነበሩ።
7 ደብዳቤውም በደረሳቸው ጊዜ፣ ሰዎቹ ሰባውን ልዑላን በሙሉ ወስደው ገደሏቸው። ራሳቸውንም በቅርጫት አድርገው ኢዩ ዘንድ ወደ ኢይዝራኤል ላኩ።
8 መልእክተኛው እንደ ደረሰም፣ ለኢዩ፣ “የንጉሡን ልጆች ራስ አምጥተዋል” ብሎ ነገረው። ከዚያም ኢዩ፣ “በከተማዪቱ መግቢያ በር ላይ ሁለት ቦታ ከምራችሁ እስከ ነገ ጧት ድረስ አቈዩአቸው” ብሎ አዘዘ።