4 በሰባተኛውም ዓመት ዮዳሄ ልኮ ካራውያንንና ዘብ ጠባቂዎቹን የሚያዙትን የመቶ አለቆች እርሱ ወዳለበት ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ እንዲመጡ አደረገ። ከእነርሱም ጋር ቃል ኪዳን በማድረግ በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ውስጥ አስማላቸው፤ ከዚያም የንጉሡን ልጅ አሳያቸው።
5 እንዲህም ሲል አዘዛቸው፤ “እናንተ የምታደርጉት ይህ ነው፤ በሦስት ምድብ ሆናችሁ በሰንበት ዕለት ዘብ ከምትጠብቁት መካከል አንዱ እጅ ቤተ መንግሥቱን ይጠብቅ፤
6 ሌላው ከሦስት አንዱ የሱርን በር ይጠብቅ፤ የቀረው ሌላው አንድ ሦስተኛው እጅ ደግሞ ቤተ መቅደሱን ተራ ገብቶ ከሚጠብቀው ከዘብ ጥበቃው ኋላ ያለውን በር ይጠብቅ።
7 እናንተ እንደተለመደው በሰንበት ዕለት ከዘብ ጥበቃ ነጻ የምትሆኑት ሁለት ሦስተኛው እጅ ግን ንጉሡ ያለበትን ቤተ መቅደስ ጠብቁ።
8 ሁላችሁም መሣሪያችሁን ይዛችሁ በንጉሡ ዙሪያ ሁኑ፤ የሚቀርባችሁ ቢኖር ግን ይገደል። ንጉሡ በሚወጣበትም ሆነ በሚገባበት ጊዜ ሁሉ አትለዩት።”
9 የመቶ አለቆቹም ካህኑ ዮዳሄ ያዘዘውን ሁሉ አደረጉ፤ እያንዳንዳቸውም በሰንበት ዕለት ለዘብ ጥበቃ የሚገቡትንና ከዘብ ጥበቃ የሚወጡትን ጭፍሮቻቸውን ይዘው ወደ ካህኑ ወደ ዮዳሄ መጡ።
10 ካህኑም በእግዚአብሔር ቤት የነበረውን የንጉሥ ዳዊትን ጦርና ጋሻ ለመቶ አለቆቹ ሰጣቸው።