1 የይሁዳ ንጉሥ የአካዝያስ ልጅ ኢዮአስ በነገሠ በሃያ ሦስተኛው ዓመት፣ የኢዩ ልጅ ኢዮአካዝ በሰማርያ ከተማ በእስራኤል ላይ ነገሠ፤ ዐሥራ ሰባት ዓመትም ገዛ።
2 እርሱም የናባጥ ልጅ ኢዮርብዓም እስራኤልን ያሳተበትን ኀጢአት በመከተል በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ሥራ ሠራ፤ ከዚህ ድርጊቱም አልተመለሰም።
3 የእግዚአብሔር ቊጣ በእስራኤል ላይ ነደደ፤ ስለዚህ የሶርያ ንጉሥ አዛሄልና ልጁ ቤንሃዳድ በነበሩበት ዘመን ሁሉ አሳልፎ በእጃቸው ሰጣቸው።
4 ከዚያም ኢዮአካዝ እግዚአብሔርን ለመነ፤ እግዚአብሔርም የሶርያ ንጉሥ እስራኤልን እንዴት አድርጎ እንዳስጨነቀ አይቶአልና ልመናውን ሰማው።
5 ስለዚህ እግዚአብሔር ለእስራኤል የሚታደጋቸውን ሰው ሰጠ፤ እነርሱም ከሶርያውያን ጭቈና ተላቀቁ፤ እንደ ቀድሞውም በየድንኳናቸው መኖር ጀመሩ፤