2 ነገሥት 15:20-26 NASV

20 ምናሔም ገንዘቡ እንዲዋጣ ያደረገው ከእስራኤል ሲሆን፣ ይህንንም ያደረገው ለአሦር ንጉሥ ይሰጥ ዘንድ እያንዳንዱ ሀብታም አምሳ፣ አምሳ ሰቅል ብር እንዲያዋጣ በማስገደድ ነበር። ስለዚህ የአሦር ንጉሥ በዚያች አገር አልቈየም፤ ተመልሶ ሄደ።

21 በምናሔም ዘመነ መንግሥት የተከናወነው ሌላው ሥራ የፈጸመውም ሁሉ በእስራኤል ነገሥታት ታሪክ ተጽፎ የሚገኝ አይደለምን?

22 ምናሔም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ ልጁ ፋቂስያስም በእግሩ ተተክቶ ነገሠ።

23 የይሁዳ ንጉሥ ዓዛርያስ በነገሠ በአምሳኛው ዓመት፣ የምናሔም ልጅ ፋቂስያስ በሰማርያ ከተማ የእስራኤል ንጉሥ ሆነ፤ ሁለት ዓመትም ገዛ።

24 ፋቂስያስ በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ነገር አደረገ፤ የናባጥ ልጅ ኢዮርብዓም፣ እስራኤልን ካሳተበት ኀጢአት አልተመለሰም።

25 ከጦር አለቆቹ አንዱ የሆነው የሮሜልዩ ልጅ ፋቁሔ አሤረበት፤ አምሳ የገለዓድ ሰዎች ይዞ በመሄድ፣ ሰማርያ ቤተ መንግሥት ባለው ምሽግ ፋቂስያስን ከአርጎብና ከአርያ ጋር ገደለው፤ በእግሩም ተተክቶ ነገሠ።

26 በፋቂስያስ ዘመነ መንግሥት የተከናወነው ሌላው ሥራ የፈጸመውም ሁሉ በእስራኤል ነገሥታት ታሪክ ተጽፎአል።