1 የሮሜልዩ ልጅ ፋቁሔ በነገሠ በዐሥራ ሰባተኛው ዓመት፣ የይሁዳ ንጉሥ፣ የኢዮአታም ልጅ አካዝ ነገሠ።
2 አካዝ ሲነግሥ ዕድሜው ሃያ ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌም ተቀምጦም ዐሥራ ስድስት ዓመት ገዛ። አባቱ ዳዊት ያደረገውን መልካም ነገር በአምላኩ በእግዚአብሔር ፊት አላደረገም።
3 እርሱም የእስራኤልን ነገሥታት መንገድ ተከተለ፤ ይልቁንም እግዚአብሔር ከእስራኤላውያን ፊት ያሳደዳቸውን የአሕዛብን ርኵሰት ተከትሎ፣ ልጁን በእሳት የሚቃጠል መሥዋዕት አድርጎ አቀረበ።
4 እንዲሁም ኰረብታ ላይ ባሉ ማምለኪያ ስፍራዎች፣ በኰረብታ አናቶችና ቅጠሉ በተንሰራፋው ዛፍ ሥር ሁሉ ሠዋ፤ ዕጣንም አጤሰ።