2 ነገሥት 16:2-8 NASV

2 አካዝ ሲነግሥ ዕድሜው ሃያ ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌም ተቀምጦም ዐሥራ ስድስት ዓመት ገዛ። አባቱ ዳዊት ያደረገውን መልካም ነገር በአምላኩ በእግዚአብሔር ፊት አላደረገም።

3 እርሱም የእስራኤልን ነገሥታት መንገድ ተከተለ፤ ይልቁንም እግዚአብሔር ከእስራኤላውያን ፊት ያሳደዳቸውን የአሕዛብን ርኵሰት ተከትሎ፣ ልጁን በእሳት የሚቃጠል መሥዋዕት አድርጎ አቀረበ።

4 እንዲሁም ኰረብታ ላይ ባሉ ማምለኪያ ስፍራዎች፣ በኰረብታ አናቶችና ቅጠሉ በተንሰራፋው ዛፍ ሥር ሁሉ ሠዋ፤ ዕጣንም አጤሰ።

5 የሶርያ ንጉሥ ረአሶንና የእስራኤል ንጉሥ የሮሜልዩ ልጅ ፋቁሔ ኢየሩሳሌምን ለመውጋትና አካዝን ለመክበብ ወጡ፤ ይሁን እንጂ ሊያሸንፉት አልቻሉም።

6 በዚያን ጊዜም የሶርያ ንጉሥ ረአሶን የይሁዳን ሰዎች አሳዶ፣ ኤላትን ወደ ሶርያ ግዛት መለሰ፤ ከዚያም ኤዶማውያን ወደ ኤላት መጥተው እስከ ዛሬ በዚያ ይኖራሉ።

7 ከዚህ የተነሣም አካዝ፣ ወደ አሦር ንጉሥ ወደ ቴልጌልቴልፌልሶር፣ “እኔ አገልጋይህም ልጅህም ነኝ፤ ስለዚህ መጥተህ ከሚወጉኝ ከሶርያ ንጉሥና ከእስራኤል ንጉሥ እጅ አድነኝ” ሲል መልእክተኞች ላከበት።

8 አካዝም በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስና በቤተ መንግሥቱ ግምጃ ቤቶች የሚገኘውን ብርና ወርቅ አውጥቶ ለአሦር ንጉሥ ገጸ በረከት ላከለት።