1 የይሁዳ ንጉሥ አካዝ በነገሠ በዐሥራ ሁለተኛው ዓመት፣ የኤላ ልጅ ሆሴዕ በሰማርያ ከተማ በእስራኤል ላይ ነገሠ፤ ዘጠኝ ዓመትም ገዛ።
2 እርሱም በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ነገር አደረገ፤ ክፉ ሥራው ግን ከእርሱ አስቀድሞ የነበሩት የእስራኤል ነገሥታት የፈጸሙትን ያህል አልነበረም።
3 የአሦር ንጉሥ ሰልም ናሶር ሊወጋው መጣ፤ ሆሴዕም ተገዛለት፤ ገበረለትም።
4 የአሦር ንጉሥ ግን ሆሴዕ እንደ ከዳው ተገነዘበ፤ ምክንያቱም ወደ ግብፅ ንጉሥ ወደ ሲጎር መልክተኞች ስለላከና በያመቱም ያደርግ እንደ ነበረው ለአሦር ንጉሥ ስላልገበረ ነው፤ ከዚህም የተነሣ ስልምናሶር ይዞ ወህኒ ቤት አስገባው።