2 ነገሥት 17:5-11 NASV

5 የአሦርም ንጉሥ አገሩን በሙሉ ወረረ፤ ወደ ሰማርያም ገሥግሦ ሦስት ዓመት ከበባት።

6 በሆሴዕ ዘመነ መንግሥት በዘጠነኛው ዓመት፣ የአሦር ንጉሥ ሰማርያን ያዘ፤ እስራኤላውያንንም በምርኮ ወደ አሦር አፈለሳቸው። እነዚህም በአላሔ፣ ጎዛን ውስጥ በአቦር ወንዝ አጠገብ እንዲሁም በሜዶን ከተሞች እንዲሰፍሩ አደረገ።

7 እንግዲህ እስራኤላውያን ይህ ሁሉ ሊደርስባቸው የቻለው፣ ከግብፅ ምድር ከፈርዖን አገዛዝ ከግብፅ ንጉሥ ያወጣቸውን አምላካቸውን እግዚአብሔርን ስለ በደሉት ነው፤ እንዲሁም ሌሎች አማልክትን በማምለክ፣

8 እግዚአብሔር ከፊታቸው አሳዶ ያወጣቸውን የአሕዛብንና የእስራኤልም ነገሥታት ወደ ምድሪቱ ያገቡትን አጸያፊ ልማድ ስለ ተከተሉ ነበር።

9 እስራኤላውያን በአምላካቸው በእግዚአብሔር ላይ ትክክል ያልሆነ ነገር በስውር አደረጉ፤ ከቃፊር መጠባበቂያ ማማ አንሥቶ እስከ ተመሸገው ከተማ ባሉት መኖሪያዎቻቸው ሁሉ በሚገኙት ኰረብቶች ላይ ማምለኪያ ስፍራዎችን ሠሩ።

10 በእያንዳንዱ ኰረብታ ላይና በእያንዳንዱም የተንሰራፋ ዛፍ ሥር ዐምደ ጣዖትና የአሼራን ምስል ዐምዶች አቆሙ።

11 እግዚአብሔር ከፊታቸው አሳዶ ያስወጣቸው አሕዛብ እንዳደረጉትም ሁሉ፣ በየኰረብታው ላይ ዕጣን አጤሱ፤ እግዚአብሔርንም የሚያስቈጣ ክፉ ነገር አደረጉ።