2 ነገሥት 17:9-15 NASV

9 እስራኤላውያን በአምላካቸው በእግዚአብሔር ላይ ትክክል ያልሆነ ነገር በስውር አደረጉ፤ ከቃፊር መጠባበቂያ ማማ አንሥቶ እስከ ተመሸገው ከተማ ባሉት መኖሪያዎቻቸው ሁሉ በሚገኙት ኰረብቶች ላይ ማምለኪያ ስፍራዎችን ሠሩ።

10 በእያንዳንዱ ኰረብታ ላይና በእያንዳንዱም የተንሰራፋ ዛፍ ሥር ዐምደ ጣዖትና የአሼራን ምስል ዐምዶች አቆሙ።

11 እግዚአብሔር ከፊታቸው አሳዶ ያስወጣቸው አሕዛብ እንዳደረጉትም ሁሉ፣ በየኰረብታው ላይ ዕጣን አጤሱ፤ እግዚአብሔርንም የሚያስቈጣ ክፉ ነገር አደረጉ።

12 እግዚአብሔር፣ “ይህን ማድረግ አይገባችሁም” ቢላቸውም እንኳ እነርሱ ጣዖታትን አመለኩ።

13 ይህም ሆኖ እግዚአብሔር፣ “ከክፉ መንገዳችሁ ተመለሱ፤ አባቶቻችሁ እንዲፈጽሙት ባዘዝኋቸው ሕግ ሁሉ መሠረት እንዲሁም በአገልጋዮቼ በነቢያት አማካይነት ለእናንተ ባስተላለፍሁት ሕግ መሠረት፣ ትእዛዜንና ሥርዐቴን ጠብቁ” ብሎ በነቢያቱና በባለ ራእዮች ሁሉ እስራኤልንና ይሁዳን አስጠንቅቆ ነበር።

14 ይሁን እንጂ እነዚህም አልሰሙም፤ እግዚአብሔር አምላካቸውን እንዳልታመኑበት እንደ አባቶቻቸው ዐንገታቸውን አደነደኑ።

15 ሥርዐቱንና ከአባቶቻቸው ጋር የገባውን ኪዳን፣ ለእነርሱም የሰጣቸውን ማስጠንቀቂያ ናቁ፤ ከንቱ ጣዖታትን ተከትለው ራሳቸውም ከንቱ ሆኑ፤ እግዚአብሔር፣ “እነርሱ የሚያደርጉትን እንዳታደርጉ” ብሎ ቢያዛቸው እንኳ በዙሪያቸው ያሉትን አሕዛብ ተከተሉ፤ እግዚአብሔር እንዳያደርጉ የከለከላቸውንም ፈጸሙ እንጂ አልተዉም።