14 ስለዚህ የይሁዳ ንጉሥ ሕዝቅያስ፣ “በደለኛው እኔ ነኝ፤ ተመለስልኝ፤ እኔም የምትጠይቀኝን ሁሉ እከፍላለሁ፤” ሲል በለኪሶ ወደ ሰፈረው ወደ አሦር ንጉሥ ይህን መልእክት ላከ። የአሦርም ንጉሥ፣ የይሁዳን ንጉሥ ሕዝቅያስን ሦስት መቶ መክሊት ብርና ሠላሳ መክሊት ወርቅ እንዲያገባለት ጠየቀው።
15 ስለዚህ ሕዝቅያስ በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስና በቤተ መንግሥቱ ግምጃ ቤቶች የሚገኘውን ብር ሁሉ ሰጠው።
16 በዚህ ጊዜም የይሁዳ ንጉሥ ሕዝቅያስ፣ በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ መዝጊያዎችና መቃኖች ላይ የለበጠውን ወርቅ ነቃቅሎ ለአሦር ንጉሥ ሰጠው።
17 የአሦርም ንጉሥ ከለኪሶ የጦሩን ጠቅላይ አዛዥ፣ ዋና አዛዡንና የጦር መሪውን ከታላቅ ሰራዊት ጋር የይሁዳ ንጉሥ ወዳለበት ወደ ኢየሩሳሌም ላከ፤ እነርሱም ወደ ኢየሩሳሌም መጥተው፣ ወደ ልብስ አጣቢው ዕርሻ በሚወስደው መንገድ ላይ የሚገኘው የላይኛው ኵሬ ውሃ በመስኖ የሚወርድበትን ስፍራ ያዙ።
18 ወደ ንጉሡም ላኩበት፤ ከዚያም የቤተ መንግሥቱ አዛዥ የሆነው የኬልቅያስ ልጅ ኤልያቄም፣ ጸሓፊው ሳምናስ እንዲሁም ታሪክ ጸሐፊው የአሳፍ ልጅ ዮአስ ወደ እነርሱ ሄደ።
19 የጦር መሪውም እንዲህ አላቸው፤ “ሕዝቅያስን እንዲህ በሉት፤“ ‘ታላቁ የአሦር ንጉሥ የሚለው ይህ ነው፤ “ለመሆኑ እንዲህ የልብ ልብ እንድታገኝ ያደረገህ ምንድ ነው?
20 የጦር ስልትና ኀይል አለኝ ትላለህ፣ ነገር ግን ወሬ ብቻ ነው። በእኔ ላይ እንዲህ ያመፅኸውስ በማን ተመክተህ ነው?