21 እነሆ፤ እንዲህ የምትመካባት ግብፅ የሚደገፍባትን ሰው እጅ ወግታ የምታቈስል የተቀጠቀጠች ሸንበቆ ናት። የግብፅ ንጉሥ ፈርዖንም ለሚመኩበት ሁሉ እንደዚሁ ነው።
22 ደግሞም፣ “የምንመካው በአምላካችን በእግዚአብሔር ነው” የምትለኝ ከሆነም፣ ሕዝቅያስ ይሁዳንና ኢየሩሳሌምን፣ “ማምለክ ያለባችሁ ኢየሩሳሌም ባለው በዚህ መሠዊያ ፊት ነው” ብሎ የኰረብታ ላይ መመለኪያዎቹንና መሠዊያዎቹን ያስፈረሰበት እርሱ አይደለምን?
23 “ ‘ከሆነልህ ከጌታዬ ከአሦር ንጉሥ ጋር ውርርድ ግጠም፤ የሚጋልቧቸው ሰዎች ማግኘት የምትችል ከሆነ፣ ሁለት ሺህ ፈረሶች እሰጥሃለሁ።
24 የምትመካው በግብፅ ሠረገሎችና ፈረሶች ሆኖ ሳለ ከጌታዬ የበታች የጦር ሹማምት እንኳ አንዱን እንዴት መመለስ ትችላለህ?
25 ከዚህም በቀር አደጋ ጥዬ ይህችን ስፍራ ለማጥፋት የመጣሁት፣ ያለ እግዚአብሔር ፈቃድ ይመስልሃል? በዚች አገር ላይ ዘምቼ እንዳጠፋት የነገረኝ ራሱ እግዚአብሔር ነው።’ ”
26 ከዚያም የኬልቅያስ ልጅ ኤልያቄም ሳምናስና ዮአስ የጦር መሪውን፣ “እኛ አገልጋዮችህ ስለ ምንሰማ፣ እባክህን በሶርያ ቋንቋ ተናገር፤ በቅጥሩ ላይ ያሉት ሰዎች በሚሰሙት በዕብራይስጥ አትናገረን” አሉት።
27 የጦር አዛዡም፣ “ለመሆኑ ጌታዬ ይህን እንድናገር የላከኝ፣ ለጌታችሁና ለእናንተ ብቻ ነውን? እነርሱም እንደ እናንተው ገና ኵሳቸውን ይበሉ ዘንድ፣ ሽንታቸውንም ይጠጡ ዘንድ በቅጥሩ ላይ ለተቀመጡት ጭምር አይደለምን?”