2 ነገሥት 18:25-31 NASV

25 ከዚህም በቀር አደጋ ጥዬ ይህችን ስፍራ ለማጥፋት የመጣሁት፣ ያለ እግዚአብሔር ፈቃድ ይመስልሃል? በዚች አገር ላይ ዘምቼ እንዳጠፋት የነገረኝ ራሱ እግዚአብሔር ነው።’ ”

26 ከዚያም የኬልቅያስ ልጅ ኤልያቄም ሳምናስና ዮአስ የጦር መሪውን፣ “እኛ አገልጋዮችህ ስለ ምንሰማ፣ እባክህን በሶርያ ቋንቋ ተናገር፤ በቅጥሩ ላይ ያሉት ሰዎች በሚሰሙት በዕብራይስጥ አትናገረን” አሉት።

27 የጦር አዛዡም፣ “ለመሆኑ ጌታዬ ይህን እንድናገር የላከኝ፣ ለጌታችሁና ለእናንተ ብቻ ነውን? እነርሱም እንደ እናንተው ገና ኵሳቸውን ይበሉ ዘንድ፣ ሽንታቸውንም ይጠጡ ዘንድ በቅጥሩ ላይ ለተቀመጡት ጭምር አይደለምን?”

28 ከዚያም የጦር አዛዡ ቆሞ ድምፁን ከፍ በማድረግ በዕብራውያን ቋንቋ እንዲህ ሲል ተናገረ፤ “እንግዲህ የታላቁን የአሦርን ንጉሥ ቃል ስሙ!

29 ንጉሡ የሚለውም ይህ ነው፤ ‘ከእጄ ሊያድናችሁ አይችልምና ሕዝቅያስ እንዳያታልላችሁ፤

30 ደግሞም ሕዝቅያስ፣ “እግዚአብሔር ያለ ጥርጥር ያድነናል፤ ይህችም ከተማ ለአሦር ንጉሥ አልፋ አትሰጥም’ በማለት በእግዚአብሔር እንድትታመኑ የሚነግራችሁን አትቀበሉ።” ’

31 “ሕዝቅያስንም አትስሙት፤ የአሦር ንጉሥ የሚለው ይህ ነው፤ ‘ከእኔ ጋር ሰላም መሥርቱ፤ እጃችሁን ስጡ፤ ከዚያም ከእናንተ እያንዳንዱ ከገዛ ወይኑና ከገዛ በለሱ ይበላል፤ ከገዛ ጒድጓዱም ውሃ ይጠጣል፤