29 ንጉሡ የሚለውም ይህ ነው፤ ‘ከእጄ ሊያድናችሁ አይችልምና ሕዝቅያስ እንዳያታልላችሁ፤
30 ደግሞም ሕዝቅያስ፣ “እግዚአብሔር ያለ ጥርጥር ያድነናል፤ ይህችም ከተማ ለአሦር ንጉሥ አልፋ አትሰጥም’ በማለት በእግዚአብሔር እንድትታመኑ የሚነግራችሁን አትቀበሉ።” ’
31 “ሕዝቅያስንም አትስሙት፤ የአሦር ንጉሥ የሚለው ይህ ነው፤ ‘ከእኔ ጋር ሰላም መሥርቱ፤ እጃችሁን ስጡ፤ ከዚያም ከእናንተ እያንዳንዱ ከገዛ ወይኑና ከገዛ በለሱ ይበላል፤ ከገዛ ጒድጓዱም ውሃ ይጠጣል፤
32 ይህም የሚሆነው የእናንተኑ ወደ ምትመስለው ምድር እህልና የወይን ጠጅ፣ ዳቦና የወይን ተክል፣ የወይራ ዛፍና ማር ወዳለበት እስካገባችሁ ድረስ ነው፤ እናንተም ሞትን ሳይሆን ሕይወትን ምረጡ።’“ሕዝቅያስ፣ ‘እግዚአብሔር ይታደገናል’ በማለት ስለሚያሳስታችሁ አትስሙት።
33 ለመሆኑ ከአሕዛብ አማልክት ምድሩን ከአሦር ንጉሥ እጅ የታደገ ማን አለ?
34 የሐማትና የአርፋድ አማልክት እስቲ የት አሉ? የሴፈርዋይም፣ የሄናና የዒዋም አማልክት ታዲያ የት ደረሱ? ሰማርያን ከእጄ አድነዋታልን?
35 ከእነዚህ አገሮች አማልክት ሁሉ አገሩን ከእኔ ለማዳን የቻለ ማን አለ? ታዲያ እግዚአብሔር ኢየሩሳሌምን ከእጄ ሊታደጋት እንዴት ይችላል?”