2 ነገሥት 19:13-19 NASV

13 ለመሆኑ የሐማትና የአርፋድ ነገሥታት የት አሉ? የሴፈርዋይም ከተማ ንጉሥስ የት አለ? ደግሞስ የሄና ወይም የዒዋ ነገሥታት የት አሉ?

14 ሕዝቅያስም ደብዳቤውን ከመልእክተኞቹ ተቀብሎ አነበበው፤ ከዚያም ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ወጥቶ ደብዳቤውን በእግዚአብሔር ፊት ዘረጋው።

15 ከዚያም ሕዝቅያስ እንዲህ ሲል ወደ እግዚአብሔር ጸለየ፤ “በኪሩቤል ላይ በዙፋንህ የተቀመጥህ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ሆይ፤ በምድር ነገሥታት ሁሉ ላይ አምላክ አንተ ብቻ ነህ፤ ሰማይንና ምድርን የፈጠርህም አንተ ነህ።

16 እግዚአብሔር ሆይ፤ አሁንም ጆሮህን አዘንብልና ስማ፤ እግዚአብሔር ሆይ፤ ዐይንህንም ክፈትና እይ፤ ሰናክሬም ሕያው እግዚአብሔርን ይሰድብ ዘንድ የላከውንም ቃል አድምጥ።

17 “እግዚአብሔር ሆይ፤ የአሦር ነገሥታት እነዚህን አሕዛብንና ምድራቸውን በርግጥ አጥፍተዋል።

18 አማልክቶቻቸውን በእሳት ውስጥ ጥለው አቃጥለዋቸዋል፤ በሰው እጅ የተሠሩ ዕንጨትና ደንጊያ ብቻ እንጂ አማልክት አልነበሩምና።

19 አሁንም እግዚአብሔር አምላካችን ሆይ፤ የምድር መንግሥታት ሁሉ እግዚአብሔር አንተ ብቻ አምላክ መሆንህን እንዲያውቁ፣ ከእጁ አድነን።”