2 ነገሥት 19:9-15 NASV

9 በዚህም ጊዜ የግብፅ ንጉሥ ኢትዮጵያዊው ቲርሐቅ፣ ሊወጋው በመገሥገሥ ላይ መሆኑን ሰናክሬም ሰማ፤ ስለዚህ ወደ ሕዝቅያስ እንደ ገና እንዲህ ሲል መልእክተኞች ላከ፤

10 “ሂዱና ለይሁዳ ንጉሥ ለሕዝቅያስ እንዲህ በሉት፤ ‘የምትመካበት አምላክ፣ “ኢየሩሳሌም በአሦር ንጉሥ እጅ አትወድቅም” በማለት እንዳያታልልህ።

11 መቼም የአሦር ነገሥታት በአገሮች ሁሉ ላይ ምን እንዳደረጉ ሰምተሃል፤ ፈጽሞ አጥፍተዋቸዋል፤ ታዲያ አንተስ ከዚህ የምታመልጥ ይመስልሃልን?

12 የቀድሞ አባቶቼ ያጠፏቸውን ሕዝቦች ማለትም ጎዛንን፣ ካራንን፣ ራፊስን እንዲሁም በተላሳር የነበሩትን የዔድንን ሰዎች አማልክታቸው አድነዋቸዋልን?

13 ለመሆኑ የሐማትና የአርፋድ ነገሥታት የት አሉ? የሴፈርዋይም ከተማ ንጉሥስ የት አለ? ደግሞስ የሄና ወይም የዒዋ ነገሥታት የት አሉ?

14 ሕዝቅያስም ደብዳቤውን ከመልእክተኞቹ ተቀብሎ አነበበው፤ ከዚያም ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ወጥቶ ደብዳቤውን በእግዚአብሔር ፊት ዘረጋው።

15 ከዚያም ሕዝቅያስ እንዲህ ሲል ወደ እግዚአብሔር ጸለየ፤ “በኪሩቤል ላይ በዙፋንህ የተቀመጥህ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ሆይ፤ በምድር ነገሥታት ሁሉ ላይ አምላክ አንተ ብቻ ነህ፤ ሰማይንና ምድርን የፈጠርህም አንተ ነህ።