2 ነገሥት 21:15-21 NASV

15 ይህን የማደርገውም የቀድሞ አባቶቻቸው ከግብፅ ምድር ከወጡበት ጊዜ አንሥቶ እስከ ዛሬ ድረስ በፊቴ ክፉ ድርጊት ስለፈጸሙና ለቊጣ ስላነሣሡኝ ነው።”

16 ይልቁንም ምናሴ፣ በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ድርጊት እንዲፈጽም ይሁዳን ካሳተበት ኀጢአት ሌላ፣ ኢየሩሳሌምን ከዳር እስከ ዳር እስኪሞላት ድረስ ብዙ ንጹሕ ደም አፈሰሰ።

17 በምናሴ ዘመነ መንግሥት የተከናወነው ሌላው ሥራ፣ የሠራውን ኀጢአት ጨምሮ የፈጸመው ድርጊት ሁሉ በይሁዳ ነገሥታት ታሪክ ተጽፎ የሚገኝ አይደለምን?

18 ምናሴም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ “የዖዛ አትክልት” በሚባለው በቤተ መንግሥቱ አትክልት ውስጥ ተቀበረ። ልጁ አሞንም በእግሩ ተተክቶ ነገሠ።

19 አሞን ሲነግሥ ዕድሜው ሃያ ሁለት ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌም ተቀምጦም ሁለት ዓመት ገዛ፤ እናቱ ሜሶላም ትባላለች፤ እርሷም የዮጥባ አገር ሰው የሐሩስ ልጅ ነበረች።

20 አባቱ ምናሴ እንዳደረገው ሁሉ እርሱም በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ድርጊት ፈጸመ።

21 አባቱ በሄደበት መንገድ ሁሉ ሄደ፤ አባቱ ያመለካቸውን አማልክት አመለከ፤ ሰገደላቸውም።