3 አባቱ ሕዝቅያስ ያፈረሰውን የየኰረብታውን ማምለኪያ ስፍራ መልሶ ሠራ፤ የእስራኤል ንጉሥ አክዓብ እንዳደረገው ሁሉ፣ እርሱም ለበኣል መሠዊያዎችን አቆመ፤ የአሼራንም ምስል ዐምድ ሠራ። እንዲሁም ለሰማይ ከዋክብት ሰራዊት ሁሉ ሰገደ፤ አመለካቸውም።
4 እግዚአብሔር፣ “ስሜን በኢየሩሳሌም አኖራለሁ” ባለበት በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ መሠዊያዎችን ሠራ።
5 በሁለቱም የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ አደባባዮች ለሰማይ ከዋክብት ሰራዊት ሁሉ መሠዊያ ሠራ።
6 የገዛ ልጁን የሚቃጠል መሥዋዕት አድርጎ አቀረበ፤ መተተኛና ጠንቋይ ሆነ፤ ሙታን አነጋጋሪዎችንና መናፍስት ጠሪዎችን ምክር ጠየቀ፤ እግዚአብሔርን ለቊጣ የሚያነሣሣውን ክፉ ድርጊት በፊቱ ፈጸመ።
7 የሠራውን የአሼራን የተቀረጸ ምስል ዐምድ ወስዶ በቤተ መቅደሱ ውስጥ አስቀመጠ፤ ይህም እግዚአብሔር ለዳዊትና ለልጁ ለሰሎሞን፣ “በዚህ ቤተ መቅደስና ከእስራኤል ነገዶች ሁሉ በመረጥኋት በኢየሩሳሌም ስሜን ለዘላለም አኖራለሁ” ያለው ስፍራ ነው።
8 እንዲሁም፤ “ብቻ ያዘዝኋቸውን ሁሉ ተጠንቅቀው በመፈጸምና ባሪያዬ ሙሴ የሰጣቸውንም ሕግ በሙሉ በመጠበቅ ይጽኑ እንጂ ከእንግዲህ የእስራኤላውያን እግር፣ ለአባቶቻቸው ከሰጠኋቸው ምድር ወጥቶ እንዲንከራተት አላደርግም” ያለው ስለ ዚሁ ስፍራ ነው።
9 ሕዝቡ ግን አልሰሙም፤ እግዚአብሔር በእስራኤላውያን ፊት ካጠፋቸው አሕዛብ ይልቅ ክፉ ድርጊት እንዲፈጽሙ ምናሴ አሳታቸው።