2 ነገሥት 23:15-21 NASV

15 እስራኤልን ባሳተው በናባጥ ልጅ በኢዮርብዓም የተሠራውን መሠዊያ፣ በቤቴል የነበረውን ያን የኰረብታ ማምለኪያ ስፍራ፣ መሠዊያው ያለበትን ያን የኰረብታ ማምለኪያ ስፍራ እንኳ እንደዚሁ አፈረሰ፤ ድንጋዮቹን ሰባበረ፤ እንደ ዱቄትም አደቀቃቸው፤ የአሼራንም ምስል ዐምድ አቃጠለ።

16 ኢዮስያስ ዘወር ሲል በኰረብታው ላይ የነበሩትን መቃብሮች አየ፤ ዐፅሞቹንም ከየመቃብሩ አስወጣ፤ ያ የእግዚአብሔር ሰው አስቀድሞ እንደ ተናገረው፣ የእግዚአብሔር ቃል ይፈጸም ዘንድ፣ መሠዊያውን ለማርከስ ሲል ዐፅሞቹን በላዩ ላይ አቃጠለበት።

17 ንጉሡም፣ “ያ የማየው የመቃብር ሐውልት የማን ነው?” ሲል ጠየቀ የከተማዪቱም ሰዎች፣ “ከይሁዳ መጥቶ አሁን አንተ ያደረግኸውን ነገር ሁሉ በቤቴል መሠዊያ ላይ እንደሚደርስ የተናገረ የዚያ የእግዚአብሔር ሰው መቃብር ነው” አሉት።

18 ኢዮስያስም፣ “በሉ እንዳለ ተዉት፤ ዐፅሙን ማንም ሰው ከቦታው እንዳያንቀሳ ቅሰው” አለ፤ ስለዚህ የእርሱንና ከሰማርያ የመጣውን ነቢይ ዐፅም ሳይነኩ እንዳለ ተውት።

19 ኢዮስያስም በቤቴል እንዳደረገው ሁሉ በሰማርያም ከተሞች ኰረብቶች ላይ የእስራኤል ነገሥታት አሠርተዋቸው የነበሩትንና እግዚአብሔርን ያስቈጡበትን ቤተ ጣዖቶች ሁሉ አስወገደ፤ አረከሳቸውም።

20 ኢዮስያስ እነዚያን የየኰረብታውን ማምለኪያ ቦታ ካህናትን ሁሉ፣ በየመሠዊያው ላይ ዐረዳቸው፤ በመሠዊያዎቹ ላይ የሰው ዐፅም አቃጠለ፣ ከዚያም ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሰ።

21 ንጉሡም መላውን ሕዝብ፣ “በዚህ በኪዳኑ መጽሐፍ በተጻፈው መሠረት የአምላካችሁን የእግዚአብሔርን ፋሲካ አክብሩ” ብሎ አዘዘ።