2 ነገሥት 23:17-23 NASV

17 ንጉሡም፣ “ያ የማየው የመቃብር ሐውልት የማን ነው?” ሲል ጠየቀ የከተማዪቱም ሰዎች፣ “ከይሁዳ መጥቶ አሁን አንተ ያደረግኸውን ነገር ሁሉ በቤቴል መሠዊያ ላይ እንደሚደርስ የተናገረ የዚያ የእግዚአብሔር ሰው መቃብር ነው” አሉት።

18 ኢዮስያስም፣ “በሉ እንዳለ ተዉት፤ ዐፅሙን ማንም ሰው ከቦታው እንዳያንቀሳ ቅሰው” አለ፤ ስለዚህ የእርሱንና ከሰማርያ የመጣውን ነቢይ ዐፅም ሳይነኩ እንዳለ ተውት።

19 ኢዮስያስም በቤቴል እንዳደረገው ሁሉ በሰማርያም ከተሞች ኰረብቶች ላይ የእስራኤል ነገሥታት አሠርተዋቸው የነበሩትንና እግዚአብሔርን ያስቈጡበትን ቤተ ጣዖቶች ሁሉ አስወገደ፤ አረከሳቸውም።

20 ኢዮስያስ እነዚያን የየኰረብታውን ማምለኪያ ቦታ ካህናትን ሁሉ፣ በየመሠዊያው ላይ ዐረዳቸው፤ በመሠዊያዎቹ ላይ የሰው ዐፅም አቃጠለ፣ ከዚያም ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሰ።

21 ንጉሡም መላውን ሕዝብ፣ “በዚህ በኪዳኑ መጽሐፍ በተጻፈው መሠረት የአምላካችሁን የእግዚአብሔርን ፋሲካ አክብሩ” ብሎ አዘዘ።

22 እስራኤልን ከመሩ ከመሳፍንት ዘመን ጀምሮ፣ በእስራኤልና በይሁዳ ነገሥታት ዘመን ሁሉ፣ እንደዚህ ያለ ፋሲካ መቼም ተከብሮ አያውቅም።

23 በኢዮስያስ ዘመነ መንግሥት በዐሥራ ስምንተኛው ዓመት ግን ይህ ፋሲካ በኢየሩሳሌም ለእግዚአብሔር ተከበረ።