2 ነገሥት 23:2-8 NASV

2 የይሁዳን ሰዎች ሁሉ፣ የኢየሩሳሌምን ከተማ ነዋሪዎች በሙሉ፣ ካህናቱንና ነቢያቱን ሁሉ ከልጅ እስከ ዐዋቂ አንድም ሰው ሳይቀር ይዞአቸው ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ መጣ። በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ የተገኘውንም የኪዳኑን መጽሐፍ ቃል በጆሮአቸው እንዲሰሙት በሙሉ አነበበላቸው።

3 ንጉሡም በዐምደ ወርቁ አጠገብ በእግዚአብሔር ፊት ቆሞ እግዚአብሔርን እንደሚከተል ትእዛዞቹን፣ ደንቦቹን፣ ሥር ዐቶቹን በፍጹም ልቡ፣ በፍጹምም ነፍሱ እንደሚጠብቅ፣ በዚህም መጽሐፍ የተጻፈውን ኪዳን እንደሚያጸና በእግዚአብሔር ፊት ኪዳኑን አደሰ፤ ከዚያም ሕዝቡ ሁሉ ለኪዳኑ ያላቸውን ታማኝነት አረጋገጡ።

4 ንጉሡም ለበኣል፣ ለአሼራና ለሰማይ ከዋክብት ሰራዊት ሁሉ የተሠሩትን የመገልገያ ዕቃዎች በሙሉ፣ ከእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ እንዲያወጡ ሊቀ ካህናቱን ኬልቅያስን በሁለተኛ ማዕረግ ያሉትን ካህናትና የቤተ መቅደሱን በር ጠባቂዎች አዘዘ። ዕቃዎቹንም ከኢየሩሳሌም ውጭ በቄድሮን ሸለቆ ሜዳ ላይ አቃጠላቸው፤ ዐመዱንም ወደ ቤቴል ወሰደው።

5 በይሁዳ ከተሞችና በኢየሩሳሌም ዙሪያ በሚገኙ ኰረብቶች ላይ ዕጣን እንዲያጥኑ የይሁዳ ነገሥታት የሾሙአቸውን የጣዖት ካህናት አባረረ እንዲሁም ለበኣል፣ ለፀሓይና ለጨረቃ፣ ለስብስብ ከዋክብትና ለመላው የሰማይ ከዋክብት ሰራዊት የሚያጥኑትን አስወገደ።

6 የአሼራንም ምስል ዐምድ ከእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ አውጥቶ ከኢየሩሳሌም ውጭ ወዳለው ወደ ቄድሮን ሸለቆ ወስዶ አቃጠለው፤ አድቅቆ ፈጭቶም በሕዝቡ መቃብር ላይ በተነው።

7 እንዲሁም ስለ አምልኮ ባዕድ ሥርዐት በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ውስጥ የቤተ ጣዖት ወንደቃዎችን ክፍሎችና ሴቶች ለአሼራ መጋረጃ የሚፈትሉባቸውን ክፍሎች አፈረሰ።

8 ኢዮስያስ የቤተ ጣዖት ካህናትን ሁሉ ከይሁዳ ከተማ ወደ ኢየሩሳሌም አወጣቸው፤ ከጌባ ጀምሮ እስከ ቤርሳቤህ ድረስ፣ ካህናቱ ዕጣን ያጥኑባቸው የነበሩትን የኰረብታ ማምለኪያ ስፍራዎችን አረከሰ። ከከተማዪቱ በር በስተ ግራ በኩል፣ በከተማዪቱ ገዥ በኢያሱ በር መግቢያ አጠገብ የነበሩትን የበሮቹን ማምለኪያ ስፍራዎች አፈረሰ።