2 ነገሥት 23:21-27 NASV

21 ንጉሡም መላውን ሕዝብ፣ “በዚህ በኪዳኑ መጽሐፍ በተጻፈው መሠረት የአምላካችሁን የእግዚአብሔርን ፋሲካ አክብሩ” ብሎ አዘዘ።

22 እስራኤልን ከመሩ ከመሳፍንት ዘመን ጀምሮ፣ በእስራኤልና በይሁዳ ነገሥታት ዘመን ሁሉ፣ እንደዚህ ያለ ፋሲካ መቼም ተከብሮ አያውቅም።

23 በኢዮስያስ ዘመነ መንግሥት በዐሥራ ስምንተኛው ዓመት ግን ይህ ፋሲካ በኢየሩሳሌም ለእግዚአብሔር ተከበረ።

24 ከዚህም በቀር ኢዮስያስ ሙታን አነጋጋሪዎችንና መናፍስት ጠሪዎችን፣ የየቤተ ሰውን አማልክት፣ ጣዖታትን እንዲሁም በይሁዳና በኢየሩሳሌም የተገኙትን ሌሎች አስጸያፊ ነገሮች ሁሉ አስወገደ፤ ይህን ያደረገውም ካህኑ ኬልቅያስ ከእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ባገኘው መጽሐፍ የተጻፈው የሕጉ ቃል ተፈጻሚነት እንዲኖረው ለማድረግ ነው።

25 በሙሴ ሕግ በተጻፈው መሠረት በፍጹም ልቡ፣ በፍጹም ነፍሱ፣ በፍጹም ኀይሉ ወደ እግዚአብሔር የተመለሰ፣ እንደ ኢዮስያስ ያለ ንጉሥ፣ ከእርሱ በፊትም ሆነ ከእርሱ በኋላ ፈጽሞ አልተነሣም።

26 ይህም ሆኖ እንኳ ለቊጣ እንዲነሣሣ ምናሴ ካደረጋቸው ነገሮች ሁሉ የተነሣ፣ እግዚአብሔር በይሁዳ ላይ ከነደደው ከአስፈሪው ቊጣው ገና አልበረደም ነበር።

27 ስለዚህ እግዚአብሔር፣ “እስራኤልን እንዳስወገድሁ ሁሉ ይሁዳንም ከፊቴ አስወግዳለሁ የመረጥኋትን ከተማ ኢየሩሳሌምንና፣ ‘ስሜ በዚያ ይሆናል’ ብዬ የተናገር ሁለትን ይህን ቤተ መቅደስ እተዋለሁ” አለ።