2 ነገሥት 23:8-14 NASV

8 ኢዮስያስ የቤተ ጣዖት ካህናትን ሁሉ ከይሁዳ ከተማ ወደ ኢየሩሳሌም አወጣቸው፤ ከጌባ ጀምሮ እስከ ቤርሳቤህ ድረስ፣ ካህናቱ ዕጣን ያጥኑባቸው የነበሩትን የኰረብታ ማምለኪያ ስፍራዎችን አረከሰ። ከከተማዪቱ በር በስተ ግራ በኩል፣ በከተማዪቱ ገዥ በኢያሱ በር መግቢያ አጠገብ የነበሩትን የበሮቹን ማምለኪያ ስፍራዎች አፈረሰ።

9 የየኰረብታው ማምለኪያ ካህናት ኢየሩሳሌም ባለው በእግዚአብሔር መሠዊያ ላይ ባያገለግሉም እንኳ ከካህናት ወንድሞቻቸው ጋር እርሾ ያልነካው ቂጣ ይበሉ ነበር።

10 በሄኖም ሸለቆ የነበረውን ቶፌት የተባለውን ማምለኪያ አረከሰ፤ ይኸውም ማንም ሰው ወንድ ወይም ሴት ልጁን ለሞሎክ በእሳት የሚቃጠል መሥዋዕት አድርጎ እንዳያቀርብበት ነው።

11 የይሁዳ ነገሥታት ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ መግቢያ ላይ ለፀሓይ አምልኮ የሰጡአቸውን ፈረሶች ከዚያ አስወገደ። እነዚህም ናታን ሜሌክ በተባለ በአንድ ሹም ቤት አጠገብ በአደባባዩ ላይ ነበሩ። ኢዮስያስም ለፀሐይ አምልኮ የተሰጡትን ሠረገሎች አቃጠለ።

12 የይሁዳ ነገሥታት በላይኛው የአካዝ እልፍኝ አጠገብ በሰገነቱ ላይ ያቆሟቸውን መሠዊያዎች፣ ምናሴም በሁለቱ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ አደባባዮች ላይ ያሠራቸውን መሠዊያዎች አስወገደ፤ ስብርብራቸውን አወጣ፤ ድቃቂውንም አንሥቶ ወደ ቄድሮን ሸለቆ ጣለው።

13 እንዲሁም ከኢየሩሳሌም በስተ ምሥራቅ ከርኵሰት ኰረብታ በስተ ደቡብ የነበሩትን የእስራኤል ንጉሥ ሰሎሞን ለሲዶናውያን የርኵሰት አምላክ ለአስታሮት፣ ለሞዓብ ሕዝቦች የርኵሰት አምላክ ለካሞሽ፣ ለአሞን ሕዝቦች የርኵሰት አምላክ ለሞሎክ ያሠራቸውን የኰረብታ ላይ ማምለኪያዎች ንጉሡ አረከሰ።

14 አሁንም ኢዮስያስ ማምለኪያ የድንጋይ ሐውልቶችን ሰባበረ፤ የአሼራን ምስል ዐምዶች ቈራረጠ፤ ስፍራውንም በሙታን ዐጥንት ሞላው።