1 በይሁዳ ንጉሥ በሴዴቅያስ ዘመነ መንግሥት በዘጠነኛው ዓመት በዐሥረኛው ወር፣ ከወሩም በዐሥረኛው ቀን የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር መላ ሰራዊቱን ይዞ ወደ ኢየሩሳሌም ዘመተ፤ ከከተማዪቱ ቅጥር ውጭ ሰፈረ፤ ዙሪያውንም በሙሉ በዕርድ ከበባት።
2 ከተማዪቱም እስከ ሴዴቅያስ ዘመነ መንግሥት ዐሥራ አንደኛ ዓመት ድረስ እንዲሁ እንደ ተከበበች ቈየች።
3 በአራተኛው ወር በዘጠነኛው ቀን በከተማዪቱ ውስጥ የተከሠተው ራብ ጸንቶ ስለ ነበር ሕዝቡ የሚቀምሰው አጣ።
4 ምንም እንኳ ባቢሎናውያን ከተማዪቱን እንደ ከበቧት ቢሆንም የከተማዪቱ ቅጥር ተጣሰ፤ ሰራዊቱም ሁሉ በንጉሡ አትክልት አጠገብ ባሉት በሁለቱ ቅጥሮች መካከል በሚገኘው በር አልፎ በሌሊት ሸሸ፤ ሽሽቱም ወደ ዮርዳኖስ ሸለቆ ነበር።
5 ይሁን እንጂ የባቢሎን ሰራዊት ንጉሡን ተከታትሎ በኢያሪኮ ሜዳ ላይ ደረሰበት። ወታደሮቹ ሁሉ ተለይተውት ተበታትነው ነበር።
6 እርሱም ተያዘ፤ በዚያን ጊዜ ሪብላ ወደ ነበረው ወደ ባቢሎን ንጉሥ አመጡት፤ ቅጣትም ተፈረደበት።
7 ሴዴቅያስ ዐይኑ እያየም የገዛ ልጆቹን ገደሉበት፤ ከዚያም ሁለት ዐይኖቹን በማውጣት በናስ ሰንሰለት አስረው ወደ ባቢሎን ወሰዱት።