2 ነገሥት 25:20-26 NASV

20 አዛዡ ናቡዘረዳንም እነዚህን ሁሉ ይዞ ልብና ወዳለው ወደ ባቢሎን ንጉሥ አመጣቸው።

21 ንጉሡም ሰዎቹን በሐማት ምድር እዚያው ልብና ውስጥ አስገደላቸው። ይሁዳም ከምድሩ በዚህ ሁኔታ ተማርኮ ሄደ።

22 የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር፣ የሳፋን የልጅ ልጅ የሆነውን የአኪቃምን ልጅ ጎዶልያስን እዚያው በቀረው በይሁዳ ሕዝብ ላይ አለቃ አድርጎ ሾመው።

23 መላው የሰራዊቱ ጦር አለቆችና ሰዎቻቸው የባቢሎን ንጉሥ፣ አገረ ገዥ አድርጎ ጎዶልያስን መሾሙን ሲሰሙ፣ እርሱ ወዳለበት ወደ ምጽጳ መጡ፤ እነርሱም የናታንያ ልጅ እስማኤል፣ የቃሬያም ልጅ ዮሐናን፣ የነጦፋዊው የተን ሑሜት ልጅ ሠራያ የማዕካታዊው ልጅ ያእዛንያና ሰዎቻቸው ነበሩ።

24 ጎዶልያስም፣ “የባቢሎናውያንን ሹማምት አትፍሩ፤ እዚሁ አገር ኑሩ፤ የባቢሎንን ንጉሥ አገልግሉ፤ ሁሉም ነገር ይሳካላችኋል” ሲል ይህንኑ በቃለ መሐላ አረጋገጠላቸው።

25 ነገር ግን በሰባተኛው ወር ንጉሣዊ ዝርያ የነበረው የኤሊሳማ የልጅ ልጅ የሆነው የናታንያ ልጅ እስማኤል ዐሥር ሰዎች ይዞ መጥቶ ጎዶልያስንና በምጽጳ አብረውት የነበሩትን የይሁዳን ሰዎችና ባቢሎናውያንን ገደለ።

26 ባቢሎናውያንን ከመፍራታቸው የተነሣም ትንሽ ትልቅ ሳይባል ሕዝቡ ሁሉ ከሰራዊቱ የጦር አለቆች ጋር ወደ ግብፅ ሸሹ።