2 ነገሥት 25:3-9 NASV

3 በአራተኛው ወር በዘጠነኛው ቀን በከተማዪቱ ውስጥ የተከሠተው ራብ ጸንቶ ስለ ነበር ሕዝቡ የሚቀምሰው አጣ።

4 ምንም እንኳ ባቢሎናውያን ከተማዪቱን እንደ ከበቧት ቢሆንም የከተማዪቱ ቅጥር ተጣሰ፤ ሰራዊቱም ሁሉ በንጉሡ አትክልት አጠገብ ባሉት በሁለቱ ቅጥሮች መካከል በሚገኘው በር አልፎ በሌሊት ሸሸ፤ ሽሽቱም ወደ ዮርዳኖስ ሸለቆ ነበር።

5 ይሁን እንጂ የባቢሎን ሰራዊት ንጉሡን ተከታትሎ በኢያሪኮ ሜዳ ላይ ደረሰበት። ወታደሮቹ ሁሉ ተለይተውት ተበታትነው ነበር።

6 እርሱም ተያዘ፤ በዚያን ጊዜ ሪብላ ወደ ነበረው ወደ ባቢሎን ንጉሥ አመጡት፤ ቅጣትም ተፈረደበት።

7 ሴዴቅያስ ዐይኑ እያየም የገዛ ልጆቹን ገደሉበት፤ ከዚያም ሁለት ዐይኖቹን በማውጣት በናስ ሰንሰለት አስረው ወደ ባቢሎን ወሰዱት።

8 የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር በነገሠ በዐሥራ ዘጠነኛው ዓመት፣ በአምስተኛው ወር ከወሩም በሰባተኛው ቀን የክብር ዘቡ ሰራዊት አዛዥና የባቢሎን ንጉሥ ከፍተኛ ባለ ሥልጣን የሆነው ናቡዘረዳን ወደ ኢየሩሳሌም መጣ።

9 የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ፣ ቤተ መንግሥቱንና በኢየሩሳሌም የሚገኙትን ቤቶች ሁሉ አቃጠለ፤ እያንዳንዱንም ታላላቅ ሕንጻ ለእሳት ዳረገው።