2 ነገሥት 3:1-7 NASV

1 የይሁዳ ንጉሥ ኢዮሣፍጥ በነገሠ በዐሥራ ስምንተኛው ዓመት፤ የአክአብ ልጅ ኢዮራም በእስራኤል ላይ በሰማርያ ነገሠ ዐሥራ ሁለት ዓመትም ገዛ።

2 እርሱም በእግዚአብሔር ፊት የተጠላ ክፉ ድርጊት ፈጸመ፤ ክፉ ድርጊቱ ግን አባትና እናቱ እንደ ፈጸሙት ዐይነት አልነበረም፤ አባቱ ያሠራውንም የበኣልን ሐውልት አስወገደ።

3 ነገር ግን የናባጥ ልጅ ኢዮርብዓም እስራኤልን ባሳተበት ኀጢአት ተያዘ፤ ከዚያም አልተላቀቀም።

4 በዚህ ጊዜ የሞዓብ ንጉሥ ሞሳ በግ ያረባ ነበር፤ እርሱም መቶ ሺህ ጠቦትና የመቶ ሺህ አውራ በግ ጠጒር ለእስራኤል ንጉሥ ይገብር ነበር።

5 አክዓብ ከሞተ በኋላ ግን የሞዓብ ንጉሥ በእስራኤል ንጉሥ ላይ ዐመፀ።

6 ስለዚህ በዚያኑ ጊዜ ንጉሥ ኢዮራም ከሰማርያ ተነሥቶ በመሄድ እስራኤልን ሁሉ አሰባሰበ።

7 ለይሁዳ ንጉሥ ለኢዮሣፍጥ፣ “የሞዓብ ንጉሥ ስለ ዐመፀብኝ አብረኸኝ ትዘምታለህን?” ሲል መልእክት ላከበት።እርሱም፣ “አዎን አብሬህ እዘምታለሁ፤ እኔ እንደ አንተው ነኝ፤ ሕዝቤ እንደ ሕዝብህ፤ ፈረሶቼም እንደ ፈረሶችህ ናቸው” በማለት መለሰለት።