18 ይህ በእግዚአብሔር ፊት ቀላል ነገር ነው። ሞዓብንም በእጃችሁ አሳልፎ ይሰጣችኋል።
19 የተመሸጉትን ከተሞችና ያማሩትን ከተሞቻቸውን ሁሉ ድል ታደርጋላችሁ። ውብ ዛፎቻቸውን ሁሉ ትቈርጣላችሁ፤ ምንጮቻቸውን በሙሉ ትደፍናላችሁ፤ መልካሙንም ዕርሻ በድንጋይ ታበላሹታላችሁ።”
20 በማግስቱ መሥዋዕት በሚቀርብበት ጊዜ፣ እነሆ፤ ከኤዶም በኩል ውሃ እየጐረፈ መጣ፤ ምድሪቱም ውሃ በውሃ ሆነች።
21 በዚህ ጊዜ ነገሥታቱ ሊወጓቸው መምጣታቸውን ሞዓባውያን ሁሉ ሰምተው ነበርና፣ ልጅም ሆነ ሽማግሌ፣ መሣሪያ መያዝ የቻለ ሁሉ ተጠርቶ በመውጣት በጠረፉ ላይ ይጠባበቅ ጀመር።
22 በማግስቱ ጠዋት ማልደው ሲነሡም፣ ፀሓይ በውሃው ላይ ታንጸባርቅ ነበር። ማዶ ላሉት ሞዓባውያንም፣ ውሃው እንደ ደም ቀልቶ ታያቸው።
23 ስለዚህ፣ “ያ እኮ ደም ነው! ያለ ጥርጥር ነገሥታቱ እርስ በርስ ተዋግተው ተራርደዋል። እንግዲህ ሞዓብ ወደ ምርኮህ ዙር!” ተባባሉ።
24 ሞዓባውያን ወደ እስራኤል ሰፈር ሲወጡም፣ እስራኤላውያን ተነሥተው ወጓቸው፤ ሞዓባውያንም ከፊታቸው ሸሹ። ከዚያም እስራኤላውያን ምድሪቱን ወረው ሞዓባውያንን ፈጇቸው።