2 ነገሥት 3:4-10 NASV

4 በዚህ ጊዜ የሞዓብ ንጉሥ ሞሳ በግ ያረባ ነበር፤ እርሱም መቶ ሺህ ጠቦትና የመቶ ሺህ አውራ በግ ጠጒር ለእስራኤል ንጉሥ ይገብር ነበር።

5 አክዓብ ከሞተ በኋላ ግን የሞዓብ ንጉሥ በእስራኤል ንጉሥ ላይ ዐመፀ።

6 ስለዚህ በዚያኑ ጊዜ ንጉሥ ኢዮራም ከሰማርያ ተነሥቶ በመሄድ እስራኤልን ሁሉ አሰባሰበ።

7 ለይሁዳ ንጉሥ ለኢዮሣፍጥ፣ “የሞዓብ ንጉሥ ስለ ዐመፀብኝ አብረኸኝ ትዘምታለህን?” ሲል መልእክት ላከበት።እርሱም፣ “አዎን አብሬህ እዘምታለሁ፤ እኔ እንደ አንተው ነኝ፤ ሕዝቤ እንደ ሕዝብህ፤ ፈረሶቼም እንደ ፈረሶችህ ናቸው” በማለት መለሰለት።

8 ኢዮሣፍጥም፣ “የምንዘምተው በየትኛው መንገድ ነው” ብሎ ጠየቀው፤ኢዮራምም “በኤዶም ምድረ በዳ አልፈን ነው” ሲል መለሰለት።

9 ስለዚህ የእስራኤል ንጉሥ ከይሁዳ ንጉሥና ከኤዶም ንጉሥ ጋር ለመዝመት ተነሣ። ሰባት ቀን ከዞሩም በኋላ ለሰራዊቱም ሆነ ለእንስሶቻቸው የተረፈ ውሃ አልነበረም።

10 የእስራኤልም ንጉሥ፣ “ወዮ! እግዚአብሔር እኛን ሦስት ነገሥታት የጠራን ለሞዓብ አሳልፎ ሊሰጠን ነውን?” አለ።