9 ሴቲቱም ባልዋን እንዲህ አለችው፤ “ይህ አዘውትሮ በደጃችን የሚያልፍ ሰው፣ ቅዱስ የእግዚአብሔር ሰው መሆኑን ዐውቃለሁ፤
10 ስለዚህ በሰገነቱ ላይ አንዲት ትንሽ ክፍል ቤት ሠርተን ዐልጋና ጠረጴዛ፣ ወንበርና ፋኖስ እናስገባለን፤ ከዚያም ወደ እኛ በሚመጣበት ጊዜ ሁሉ ማረፊያ ትሆነዋለች።”
11 አንድ ቀን ኤልሳዕ ወደዚያው መጥቶ ወደ ማረፊያ ክፍሉ በመውጣት ጋደም አለ።
12 አገልጋዩን ግያዝንም፣ “ሱነማዪቱን ጥራት” አለው፤ በጠራትም ጊዜ መጥታ በፊቱ ቆመች።
13 ኤልሳዕም፣ “ ‘ለእኛ ስትይ በጣም ተቸግረሻል፣ ምን እንዲደረግልሽ ትፈልጊአለሽ? ለንጉሡ ወይስ ለሰራዊቱ አዛዥ የምንነግርልሽ ጒዳይ አለን?’ ብለህ ጠይቃት” አለው።ሴቲቱም መልሳ፣ “እኔ እኮ የምኖረው በገዛ ወገኖቼ መካከል ነው” አለችው።
14 ኤልሳዕም፣ “ታዲያ ምን ይደረግላት” ሲል ጠየቀ።ግያዝም፣ “ልጅ እኮ የላትም፤ ባሏም ሸምግሎአል” አለ።
15 ኤልሳዕም፣ “በል እንግዲያው ጥራት” አለው፤ እርሱም ጠርቶአት መጥታ እበራፉ ላይ ቆመች።