2 ነገሥት 5:1-7 NASV

1 በዚህ ጊዜ ንዕማን የሶርያ ንጉሥ ጦር አዛዥ ነበረ፤ እግዚአብሔር በዚህ ሰው አማካይነት፣ ሶርያ ድልን እንድትጐናጸፍ ስላደረጋት በጌታው ዘንድ ታላቅና የተከበረ ሰው ነበር። ጀግና ወታደር ቢሆንም ለምጽ ወጥቶበት ነበር።

2 አደጋ ጣዮች ከሶርያ ወጥተው፣ ከእስራኤል ምድር አንዲት ልጃገረድ ማረኩ፤ እርሷም የንዕማንን ሚስት ታገለግላት ነበር።

3 እመቤቷንም፣ “ጌታዬ በሰማርያ ያለውን ነቢይ ሄዶ ቢያገኘው እኮ ከዚህ ለምጹ ይፈውሰው ነበር” አለቻት።

4 ንዕማንም ወደ ጌታው ሄዶ ከእስራኤል የመጣችው ልጃገረድ ያለችውን ነገረው።

5 የሶርያም ንጉሥ፣ “በል እንግዲያው አሁኑኑ ሂድ፤ እኔም ለእስራኤል ንጉሥ ደብዳቤ እጽፋለሁ” አለው፤ ስለዚህ ንዕማን ዐሥር መክሊት ብር፣ ስድስት ሺህ ሰቅል ወርቅና ዐሥር ሙሉ ልብስ ይዞ ሄደ።

6 ለእስራኤልም ንጉሥ የያዘው ደብዳቤ፣ “ከለምጹ እንድትፈውሰው ይህን ደብዳቤ አስይዤ አገልጋዬን ንዕማንን ወዳንተ ልኬዋለሁ” የሚል ነው።

7 የእስራኤልም ንጉሥ ደብዳቤውን ወዲያው እንዳነበበ ልብሱን ቀዶ፣ “ለምጽ እንድ ፈውሰው ይህን ሰው ወደ እኔ መላኩ እኔ ገድዬ ማዳን የምችል አምላክ ሆኜ ነውን? እንግዲህ ጠብ ሲፈልገኝ እዩ!” አለ።