21 የእስራኤልም ንጉሥ ባያቸው ጊዜ፣ “አባቴ ሆይ፤ ልግደላቸውን? ልፍጃቸውን?” ብሎ ኤልሳዕን ጠየቀው።
22 እርሱም፣ “አትግደላቸው፤ ለመሆኑ በሰይፍህና በቀስትህ የማረክሃቸውን ትገድላቸው ዘንድ ይገባሃልን? አሁንም የሚበሉትንና የሚጠጡትን አስቀርብላቸው፤ በልተው ጠጥተውም ወደ ጌታቸውም ይሂዱ” አለው።
23 ስለዚህ ታላቅ ግብዣ አዘጋጅቶላቸው ከበሉና ከጠጡ በኋላ አሰናብቶአቸው ወደ ጌታቸው ሄዱ። የሶርያ አደጋ ጣዮችም የእስራኤልን ምድር ለመውረር ከዚያ በኋላ አልተመለሱም።
24 ከጥቂት ጊዜ በኋላም የሶርያ ንጉሥ ቤን ሐዳድ ሰራዊቱን ሁሉ ሰበሰበ፤ ወጥቶም ሰማርያን ከበባት።
25 ከተማዪቱን እንደ ከበባትም የአንድ አህያ ጭንቅላት በሰማኒያ ሰቅል ብር፣ የጎሞር አንድ ስምንተኛ የርግብ ኵስ በአምስት ሰቅል ብር እስኪ ሸጥ ድረስ ታላቅ ራብ ሆነ።
26 የእስራኤልም ንጉሥ በቅጥሩ ላይ በሚመላለስበት ጊዜ አንዲት ሴት ድምፅዋን ከፍ አድርጋ “ጌታዬ፣ ንጉሥ ሆይ፤ እባክህ ርዳኝ!” አለች።
27 ንጉሡም፣ “እግዚአብሔር ካልረዳሽ እኔ እንዴት ልረዳሽ እችላለሁ? ከዐውድማው ነው ወይስ ከወይን መጥመቂያው የምረዳሽ?” ሲል መለሰላት።