2 ነገሥት 6:25-31 NASV

25 ከተማዪቱን እንደ ከበባትም የአንድ አህያ ጭንቅላት በሰማኒያ ሰቅል ብር፣ የጎሞር አንድ ስምንተኛ የርግብ ኵስ በአምስት ሰቅል ብር እስኪ ሸጥ ድረስ ታላቅ ራብ ሆነ።

26 የእስራኤልም ንጉሥ በቅጥሩ ላይ በሚመላለስበት ጊዜ አንዲት ሴት ድምፅዋን ከፍ አድርጋ “ጌታዬ፣ ንጉሥ ሆይ፤ እባክህ ርዳኝ!” አለች።

27 ንጉሡም፣ “እግዚአብሔር ካልረዳሽ እኔ እንዴት ልረዳሽ እችላለሁ? ከዐውድማው ነው ወይስ ከወይን መጥመቂያው የምረዳሽ?” ሲል መለሰላት።

28 ከዚያም፣ “ለመሆኑ ችግርሽ ምንድ ነው?” ሲል ጠየቃት።እርሷም እንዲህ ስትል መለሰችለት፤ “ይህች ሴት፣ ‘ዛሬ እንድንበላው ልጅሽን አምጪው፤ ነገ ደግሞ የእኔን ልጅ እንበላዋለን’ አለችኝ።

29 ስለዚህ ልጄን ቀቅለን በላነው። በማግሥቱም፣ ‘እንድንበላው ልጅሽን አምጪው’ አልኋት፤ እርሷ ግን ደበቀችው።”

30 ንጉሡም ሴቲቱ ያለችውን ሲሰማ ልብሱን ቀደደ፤ በቅጥሩ ላይ በሚመላለስበትም ጊዜ በውስጥ ማቅ መልበሱን ሕዝቡ አየ።

31 ንጉሡም፣ “የሣፋጥ ልጅ የኤልሳዕ ራስ ዛሬ በዐንገቱ ላይ ካደረ፣ እግዚአብሔር ይህን ያድርግብኝ፤ ከዚህም የባሰ ያምጣብኝ” ብሎ ዛተ።