2 ነገሥት 6:26-32 NASV

26 የእስራኤልም ንጉሥ በቅጥሩ ላይ በሚመላለስበት ጊዜ አንዲት ሴት ድምፅዋን ከፍ አድርጋ “ጌታዬ፣ ንጉሥ ሆይ፤ እባክህ ርዳኝ!” አለች።

27 ንጉሡም፣ “እግዚአብሔር ካልረዳሽ እኔ እንዴት ልረዳሽ እችላለሁ? ከዐውድማው ነው ወይስ ከወይን መጥመቂያው የምረዳሽ?” ሲል መለሰላት።

28 ከዚያም፣ “ለመሆኑ ችግርሽ ምንድ ነው?” ሲል ጠየቃት።እርሷም እንዲህ ስትል መለሰችለት፤ “ይህች ሴት፣ ‘ዛሬ እንድንበላው ልጅሽን አምጪው፤ ነገ ደግሞ የእኔን ልጅ እንበላዋለን’ አለችኝ።

29 ስለዚህ ልጄን ቀቅለን በላነው። በማግሥቱም፣ ‘እንድንበላው ልጅሽን አምጪው’ አልኋት፤ እርሷ ግን ደበቀችው።”

30 ንጉሡም ሴቲቱ ያለችውን ሲሰማ ልብሱን ቀደደ፤ በቅጥሩ ላይ በሚመላለስበትም ጊዜ በውስጥ ማቅ መልበሱን ሕዝቡ አየ።

31 ንጉሡም፣ “የሣፋጥ ልጅ የኤልሳዕ ራስ ዛሬ በዐንገቱ ላይ ካደረ፣ እግዚአብሔር ይህን ያድርግብኝ፤ ከዚህም የባሰ ያምጣብኝ” ብሎ ዛተ።

32 በዚህ ጊዜ ኤልሳዕ በቤቱ ተቀምጦ ነበር፤ ሽማግሌዎችም አብረውት ተቀምጠው ነበር። ንጉሡም መልእክተኛ ቀድሞት እንዲሄድ አደረገ። የተላከውም ሰው ከመድረሱ በፊት ኤልሳዕ ለሽማግሌዎቹ፣ “ይህ ነፍሰ ገዳይ ራሴን ለመቊረጥ ሰው መላኩን ታያላችሁ? እነሆ፤ አሁንም መልእክተኛው ሲደርስ በሩን ዘግታችሁ እንዳይገባ አድርጉ። የጌታው የእግሩ ኮቴ ከኋላው ይሰማ የለምን?” አላቸው።