2 ነገሥት 7:9-15 NASV

9 እርስ በርሳቸውም፣ “ያደረግነው ትክክል አይደለም፤ ዕለቱ የምሥራች ቀን ነው፤ እኛ ግን የራሳችን ብቻ አደረግነው፤ እስኪነጋም ከቈየን በደለኞች እንሆናለን፤ ስለዚህ ወደ ቤተ መንግሥት በፍጥነት ሄደን እንንገር” ተባባሉ።

10 ስለዚህ ሄደው የከተማዪቱን መግቢያ በር ጠባቂዎች ጮኸው በመጥራት፣ “ወደ ሶርያውያን ሰፈር ገባን፤ እዚያም ከታሰሩ ፈረሶችና አህዮች በቀር አንድም ሰው አልነበረም፤ የማንም ድምፅ አልተሰማም፤ ድንኳኖቹም እንዳሉ ናቸው” ብለው ነገሯአቸው።

11 የበሩ ጠባቂዎችም ይህንኑ አስተጋቡ፤ ዜናውም በቤተ መንግሥቱ ተሰማ።

12 ንጉሡም በሌሊት ተነሥቶ ለጦር አለቆቹ እንዲህ አላቸው፤ “ሶርያውያን ያደረጉብንን እነግራችኋለሁ፤ መራባችንን ስለሚያውቁ፣ ‘መቼም መውጣታቸው አይቀርም፤ ከዚያም ከነሕይወታቸው እንማርካቸዋለን፤ እኛም ሰተት ብለን ወደ ከተማዪቱ እንገባለን’ በማለት በገጠር ለመደበቅ ከሰፈራቸው ወጥተዋል።”

13 ከጦር አለቆቹም አንዱ እንዲህ አለ፤ “ጥቂት ሰዎች በከተማዪቱ ውስጥ ከተረፉት ፈረሶች አምስቱን ይዘው ይሂዱ፤ ዕጣ ፈንታቸውም በዚህ ከቀሩት እስራኤላውያን ሁሉ ዕድል ጋር አንድ ነው፤ የሚጠብቃቸው ቢኖር በዚህ በሙሉ እንዳለቁት እስራኤላውያን መሆን ብቻ ነው፤ ስለዚህ እንላካቸውና የሆነውን እንይ።”

14 ስለዚህ ሁለት ሠረገሎች ከነፈረሶቻቸው መረጡ፤ ንጉሡም፣ “ሂዱና የሆነውን ነገር እዩ” ብሎ ከሶርያውያን ሰራዊት በኋላ እንዲሄዱ ላካቸው።

15 እነርሱም እስከ ዮርዳኖስ ድረስ ተከተሏቸው። ሶርያውያን በጥድፊያ ሲሸሹ፣ የጣሉትንም ልብስና ዕቃ በየመንገዱ ላይ ተበታትኖ አገኙ፤ መልክተኞቹም ተመልሰው ይህንኑ ለንጉሡ ነገሩት።