1 በዚህ ጊዜ ኤልሳዕ፣ ልጇ ከሞት ያስነሣላትን ሴት፣ “እግዚአብሔር በምድሪቱ ላይ የሰባት ዓመት ራብ ስለ ወሰነ፣ ተነሺና ለጊዜው መቈየት ወደምትችዪበት ቦታ ከቤተሰብሽ ጋር ሂጂ” አላት።
2 ሴቲቱም ተነሥታ የእግዚአብሔር ሰው እንደ ነገራት አደረገች፤ ከነቤተ ሰቧም ሄዳ፣ በፍልስጥኤም ምድር ሰባት ዓመት ተቀመጠች።
3 ከሰባት ዓመት በኋላም፣ ከፍልስጥኤም ምድር ተመልሳ መጣች፤ ስለ ቤቷና ስለ መሬቷ አቤቱታ ለማቅረብ፣ ወደ ንጉሡ ሄደች።
4 በዚህ ጊዜ ንጉሡ የእግዚአብሔርን ሰው አገልጋይ ግያዝን፣ “ኤልሳዕ ያደረጋቸውን ታላላቅ ሥራዎች ሁሉ እስቲ ንገረኝ” እያለው ነበር።
5 ኤልሳዕ ልጇን ከሞት ያስነሣላት ሴት ስለ ቤቷና ስለ መሬቷ ለማመልከት ወደ ንጉሡ ዘንድ የቀረበችውም፣ ኤልሳዕ የሞተውን ልጅ እንዴት እንዳስነሣ፣ ግያዝ ለንጉሡ በሚነግርበት ወቅት ነበር።ግያዝም፣ “ንጉሥ ጌታዬ ሆይ፤ ሴቲቱ ይህች ናት፤ ኤልሳዕ ከሞት ያስነሣው ልጇም ይህ ነው” አለ።
6 ንጉሡም ስለ ዚሁ ጒዳይ ጠየቃትና ነገረችው።ከዚያም ንጉሡ፣ “የነበራትን ሁሉ እንዲሁም ትታ ከሄደችበት ጊዜ አንሥቶ እስካሁን ድረስ ያለውን የዕርሻዋን ሰብል በሙሉ እንድትመልስላት” ሲል አንድ ሹም አዘዘላት።
7 ኤልሳዕ ወደ ደማስቆ ሄደ፤ በዚያን ጊዜም የሶርያ ንጉሥ ቤንሃዳድ ታሞ ነበር፤ ለንጉሡም፣ “የእግዚአብሔር ሰው ወደዚህ መጥቶአል ብለው ነገሩት።