2 ነገሥት 8:15-21 NASV

15 በማግስቱ ግን ወፍራም ልብስ ወስዶ በውሃ ከነከረ በኋላ የንጉሡን ፊት ሸፈነው፤ ንጉሡም በዚሁ ሞተ፤ ከዚያም አዛሄል በእግሩ ተተክቶ ነገሠ።

16 የእስራኤል ንጉሥ የአክዓብ ልጅ ኢዮራም በነገሠ በአምስተኛው ዓመት፣ የኢዮሣፍጥ ልጅ ኢዮሆራም በይሁዳ ነገሠ።

17 እርሱም ሲነግሥ ዕድሜው ሠላሳ ሁለት ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌም ተቀምጦም ስምንት ዓመት ገዛ።

18 ያገባት የአክዓብ ልጅ ስለ ነበረች የአክዓብ ቤት እንዳደረገው ሁሉ፣ እርሱም የእስራኤልን ነገሥታት መንገድ ተከተለ፤ በእግዚአብሔርም ፊት ክፉ ድርጊት ፈጸመ።

19 ይሁን እንጂ ስለ ባሪያው ስለ ዳዊት ሲል፣ እግዚአብሔር ይሁዳን ሊያጠፋ አልፈለገም፤ ምክንያቱም ለዳዊትና ለዘሩ መብራት እንደማያሳጣ ተስፋ ሰጥቶ ነበርና።

20 በኢዮሆራም ዘመነ መንግሥት፣ ኤዶምያስ በይሁዳ ላይ ዐምፆ የራሱን ንጉሥ አነገሠ።

21 ስለዚህም ኢዮሆራም ሠረገሎቹን ሁሉ አሰልፎ ወደ ጸዒር ዘመተ። ኤዶማውያንም እርሱንና የሠረገላ አዛዦቹን ከበቡ፤ እርሱና የሠረገላ አዛዦቹ ግን በሌሊት ተነሥተው ከበባውን ጥሰው ወጡ፤ ሰራዊቱም ሸሽቶ ተመለሰ።