2 ነገሥት 9:17-23 NASV

17 በኢይዝራኤል ግንብ ማማ ላይ የቆመው ጠባቂ የኢዩ ወታደሮች መቅረባቸውን አይቶ፣ “ኧረ ወታደሮች መጡ” በማለት ጮኾ ተናገረ።ኢዮራምም፣ “አንድ ፈረሰኛ ተጠርቶ፤ እንዲገናኛቸው ላኩትና፣ ‘የመጣችሁት በሰላም ነውን?’ ብሎ ይጠይቅ” ሲል አዘዘ።

18 ፈረሰኛውም ኢዩን ለመገናኘት ጋልቦ ሄደና፣ “ንጉሡ፣ ‘የመጣችሁት በሰላም ነውን?’ ብሎአል” አለው።ኢዩም፣ “ስለ ሰላም መጨነቅ የአንተ ጒዳይ አይደለም! ይልቅስ ወደ ኋላ እለፍና ተከተለኝ” አለው።ጠባቂውም፣ “መልእክተኛው ከእነርሱ ዘንድ ደርሶአል፤ ነገር ግን ተመልሶ አልመጣም” ብሎ አሳወቀ።

19 ስለዚህ ንጉሡ ሌላ ፈረሰኛ ላከ፤ ወደ እነርሱ ዘንድ እንደ ደረሰም፣ “ንጉሡ፣ ‘የመጣችሁት በሰላም ነውን?’ ይላል” አለው።ኢዩም “ስለ ሰላም መጨነቅ የአንተ ጒዳይ አይደለም! ይልቅስ ወደ ኋላ እለፍና ተከተለኝ” አለው።

20 ጠባቂው፣ “መልእክተኛው ከእነርሱ ዘንድ ደርሶአል፤ ነገር ግን ይህም ተመልሶ አልመጣም፤ የወታደሮቹ መሪ ሠረገላ አነዳዱ ልክ እንደ ናሜሲ ልጅ እንደ ኢዩ አነዳድ ነው፤ ሲነዳም እንደ እብድ ነው” ሲል አሳወቀ።

21 ኢዮራምም፣ “በሉ ሠረገላዬን አዘጋጁ” ብሎ አዘዘ። ሠረገላው እንደ ተዘጋጀም፣ የእስራኤል ንጉሥ ኢዮራምና የይሁዳ ንጉሥ አካዝያስ በየሠረገሎቻቸው ሆነው ኢዩን ለመገናኘት ሄዱ፤ የኢይዝራኤላዊው የናቡቴ ርስት በነበረው ዕርሻ ላይም ተገናኙት።

22 ኢዮራምም ኢዩን ገና ሲያየው፣ “ኢዩ፣ የመጣኸው በሰላም ነውን?” ሲል ጠየቀው።ኢዩም፣ “የእናትህ የኤልዛቤል የጣዖት አምልኮና መተት እንዲህ በዝቶ እያለ ምን ሰላም አለ!” ሲል መለሰ።

23 ኢዮራምም ሠረገላውን አዙሮ በመሸሽ፣ “አካዝያስ ሆይ፤ ይህ ክዳት ነው!” አለ።