2 ነገሥት 9:20-26 NASV

20 ጠባቂው፣ “መልእክተኛው ከእነርሱ ዘንድ ደርሶአል፤ ነገር ግን ይህም ተመልሶ አልመጣም፤ የወታደሮቹ መሪ ሠረገላ አነዳዱ ልክ እንደ ናሜሲ ልጅ እንደ ኢዩ አነዳድ ነው፤ ሲነዳም እንደ እብድ ነው” ሲል አሳወቀ።

21 ኢዮራምም፣ “በሉ ሠረገላዬን አዘጋጁ” ብሎ አዘዘ። ሠረገላው እንደ ተዘጋጀም፣ የእስራኤል ንጉሥ ኢዮራምና የይሁዳ ንጉሥ አካዝያስ በየሠረገሎቻቸው ሆነው ኢዩን ለመገናኘት ሄዱ፤ የኢይዝራኤላዊው የናቡቴ ርስት በነበረው ዕርሻ ላይም ተገናኙት።

22 ኢዮራምም ኢዩን ገና ሲያየው፣ “ኢዩ፣ የመጣኸው በሰላም ነውን?” ሲል ጠየቀው።ኢዩም፣ “የእናትህ የኤልዛቤል የጣዖት አምልኮና መተት እንዲህ በዝቶ እያለ ምን ሰላም አለ!” ሲል መለሰ።

23 ኢዮራምም ሠረገላውን አዙሮ በመሸሽ፣ “አካዝያስ ሆይ፤ ይህ ክዳት ነው!” አለ።

24 ከዚያም ኢዩ ቀስቱን በማስፈንጠር ኢዮራምን በትከሻና ትከሻው መካከል ወጋው፤ ፍላጻውም ዘልቆ ልቡን ስለ ወጋው፣ ሠረገላው ውስጥ ዘፍ ብሎ ወደቀ።

25 ኢዩም የሠረገላ ኀላፊውን ቢድቃርን እንዲህ አለው፤ “አንሣውና በኢይዝራኤላዊው በናቡቴ ዕርሻ ላይ ጣለው፤ አንተና እኔ አባቱን አክዓብን በየሠረገሎቻችን ሆነን ተከትለነው ስንሄድ፣ እግዚአብሔር ይህን ትንቢት እንዲህ ሲል እንደ ተናገረበት አስታውስ፤

26 ‘ትናንት የናቡቴንና የልጆቹን ደም አይቻለሁ፤ ይላል እግዚአብሔር፤ ይህንንም በዚሁ ዕርሻ ላይ በርግጥ አንተው እንድትከፍል አደርግሃለሁ፤ ይላል እግዚአብሔር፤’ አሁንም በእግዚአብሔር ቃል በተነገረው መሠረት አንሣውና በዚሁ ዕርሻ ውስጥ ጣለው።”