1 ሮብዓም መንግሥቱን ከመሠረተና ካጸና በኋላ እርሱና እስራኤል ሁሉ የእግዚአብሔርን ሕግ ተዉ።
2 እግዚአብሔርን ከመበደላቸው የተነሣም፣ ሮብዓም በነገሠ በአምስተኛው ዓመት የግብፅ ንጉሥ ሺሻቅ በኢየሩሳሌም ላይ ዘመተ።
3 ከግብፅ አብረውት የመጡትን ዐሥራ ሁለት ሺህ ሠረገላዎች፣ ስድሳ ሺ ፈረሰኞችና ስፍር ቊጥር የሌላቸውን የሊብያ፣ የሱኪምና የኢትዮጵያ ወታደሮችን ይዞ፣
4 የተመሸጉትን የይሁዳ ከተሞች በቁጥጥሩ ሥር በማድረግ እስከ ኢየሩሳሌም ዘለቀ።
5 ከዚህ በኋላ ነቢዩ ሸማያ ወደ ሮብዓምና ሺሻቅን ፈርተው በኢየሩሳሌም ወደ ተሰበሰቡት ወደ እስራኤል መሪዎች መጥቶ፣ “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘እናንተ ትታችሁኛል፤ ስለዚህ እኔም በሺሻቅ እጅ ትቼአችኋለሁ’ ” አላቸው።