2 ዜና መዋዕል 12:1-7 NASV

1 ሮብዓም መንግሥቱን ከመሠረተና ካጸና በኋላ እርሱና እስራኤል ሁሉ የእግዚአብሔርን ሕግ ተዉ።

2 እግዚአብሔርን ከመበደላቸው የተነሣም፣ ሮብዓም በነገሠ በአምስተኛው ዓመት የግብፅ ንጉሥ ሺሻቅ በኢየሩሳሌም ላይ ዘመተ።

3 ከግብፅ አብረውት የመጡትን ዐሥራ ሁለት ሺህ ሠረገላዎች፣ ስድሳ ሺ ፈረሰኞችና ስፍር ቊጥር የሌላቸውን የሊብያ፣ የሱኪምና የኢትዮጵያ ወታደሮችን ይዞ፣

4 የተመሸጉትን የይሁዳ ከተሞች በቁጥጥሩ ሥር በማድረግ እስከ ኢየሩሳሌም ዘለቀ።

5 ከዚህ በኋላ ነቢዩ ሸማያ ወደ ሮብዓምና ሺሻቅን ፈርተው በኢየሩሳሌም ወደ ተሰበሰቡት ወደ እስራኤል መሪዎች መጥቶ፣ “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘እናንተ ትታችሁኛል፤ ስለዚህ እኔም በሺሻቅ እጅ ትቼአችኋለሁ’ ” አላቸው።

6 የእስራኤል መሪዎችና ንጉሡ ራሳቸውን በማዋረድ፣ “እግዚአብሔር ጻድቅ ነው” አሉ።

7 እግዚአብሔርም ራሳቸውን እንዳዋረዱ ባየ ጊዜ፣ የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል ወደ ሸማያ መጣ፤ “ራሳቸውን ዝቅ አድርገው ስላዋረዱ እታደጋቸዋለሁ እንጂ አላጠፋቸውም፤ ቊጣዬም በሺሻቅ እጅ በኢየሩሳሌም ላይ አይፈስስም።