6 የእስራኤል መሪዎችና ንጉሡ ራሳቸውን በማዋረድ፣ “እግዚአብሔር ጻድቅ ነው” አሉ።
7 እግዚአብሔርም ራሳቸውን እንዳዋረዱ ባየ ጊዜ፣ የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል ወደ ሸማያ መጣ፤ “ራሳቸውን ዝቅ አድርገው ስላዋረዱ እታደጋቸዋለሁ እንጂ አላጠፋቸውም፤ ቊጣዬም በሺሻቅ እጅ በኢየሩሳሌም ላይ አይፈስስም።
8 ይሁን እንጂ እኔን በማገልገልና የሌሎችን አገሮች ነገሥታት በማገልገል መካከል ያለውን ልዩነት ያውቁ ዘንድ፣ ለእርሱ ይገዛሉ።”
9 የግብፅ ንጉሥ ሺሻቅ ኢየሩሳሌምን በወረረ ጊዜ፣ የቤተ መቅደሱን ንብረትና የቤተ መንግሥቱን ንብረት ዘርፎ ወሰደ፤ ሰሎሞን ያሠራው የወርቅ ጋሻ ሳይቀር፣ እንዳለ ሁሉንም አጋዘው።
10 ንጉሥ ሮብዓምም በተወሰዱት ፈንታ የናስ ጋሻዎች ሠርቶ፤ የቤተ መንግሥቱን ቅጥር በሮች ለሚጠብቁ የዘብ አለቆች በኀላፊነት ሰጠ።
11 ንጉሡ ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ በሚሄድበት ጊዜ ሁሉ፣ ዘበኞቹ ጋሻዎቹን አንግበው ያጅቡት ነበር፤ ከዚያም በኋላ ጋሻዎቹን ወደ ዘበኞች ክፍል ይመልሱ ነበር።
12 ሮብዓም ራሱን ዝቅ አድርጎ ስላዋረደ የእግዚአብሔር ቊጣ ከእርሱ ተመለሰ፤ ፈጽሞም አላጠፋውም፤ በይሁዳም ደግሞ በጥቂቱም ቢሆን መልካም ነገር ተገኝቶ ነበር።