2 ዜና መዋዕል 13:2-8 NASV

2 በኢየሩሳሌም ተቀምጦም ሦስት ዓመት ገዛ። እናቱ ሚካያ ትባላለች፤ እርሷም የገብዓ ተወላጅ የኡርኤል ልጅ ነበረች።በአብያና በኢዮርብዓምም መካከል ጦርነት ነበር።

3 አብያ አራት መቶ ሺህ ብርቱ ተዋጊዎች ይዞ ዘመተ፤ ኢዮርብዓምም ስምንት መቶ ሺህ ብርቱ ተዋጊዎች ይዞ በመውጣት ጠበቀው።

4 አብያ በኰረብታማው በኤፍሬም አገር በጽማራይም ተራራ ላይ ቆሞ፣ እንዲህ አለ፤ “ኢዮርብዓምና እስራኤል ሁሉ አድምጡኝ!

5 የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ዳዊትና ዘሮቹ በእስራኤል ላይ ለዘላለም እንዲነግሡ በጨው ኪዳን የሰጣቸው መሆኑን አታውቁምን?

6 የዳዊት ልጅ የሰሎሞን ባሪያ የነበረው የናባጥ ልጅ ኢዮርብዓም ግን በጌታው ላይ ዐመፀ።

7 የሰሎሞን ልጅ ሮብዓም ገና ሕፃን ሳለ፣ ምንም ማድረግ በማይችልበትና እነርሱንም ለመቋቋም አቅሙ በማይፈቅድለት ጊዜ የማይረቡ ጥቂት ወሮበሎች በዙሪያው ተሰበሰቡበት፣ በረቱበትም።

8 “አሁንም እናንተ በዳዊት ዘርዐ-ትውልድ እጅ ያለውን የእግዚአብሔርን መንግሥት ልትቋቋሙ አስባችኋል። በእርግጥም በሰራዊት ረገድ እጅግ ብዙ ናችሁ፤ አማልክቶቻችሁ ይሆኑ ዘንድ ኢዮርብዓም የሠራቸውንም የወርቅ ጥጆች ይዛችኋል።