2 አሳም ከእግዚአብሔር ቤተ መቅደስና ከራሱም ቤተ መንግሥት ግምጃ ቤቶች ብርና ወርቅ ወስዶ በደማስቆ ተቀምጦ ይገዛ ለነበረው ለሶርያ ንጉሥ ለወልደ አዴር ላከ፤
3 ከዚያም “ቀድሞ በአባቴና በአባትህ መካከል እንደ ነበረው ሁሉ፣ ዛሬም በእኔና በአንተ መካከል የስምምነት ውል ይኑረን፤ እነሆ፤ ብርና ወርቅ ልኬልሃለሁ፤ ከእኔ ተመልሶ ይሄድ ዘንድ ከባኦስ ጋር ያደረግኸውን የስምምነት ውል አፍርስ” አለው።
4 ወልደአዴር የንጉሥ አሳን ሐሳብ ተቀበለ፤ የጦር አዛዦቹንም በእስራኤል ከተሞች ላይ አዘመተ። እነርሱ ዒዮንን፣ ዳንን፣ አቤልማ ይምንና የንፍታሌምን የዕቃ ግምጃ ቤት ከተሞች ሁሉ ድል አድርገው ያዙ።
5 ባኦስ ይህን በሰማ ጊዜ ራማን መገንባቱን አቆመ፤ ሥራውንም አቋረጠ።
6 ንጉሥ አሳም የይሁዳን ሰዎች ሁሉ አመጣቸው፤ እነርሱም ባኦስ ይሠራበት የነበረውን ድንጋይና እንጨት ወሰዱ፤ አሳም ጌባንና ምጽጳን ሠራባት።
7 በዚያን ጊዜም ባለ ራእዩ አናኒ ወደ ይሁዳ ንጉሥ ወደ አሳ መጥቶ እንዲህ አለው፤ “በአምላክህ በእግዚአብሔር ሳይሆን በሶርያ ንጉሥ ስለ ታመንህ፣ የሶርያ ንጉሥ ሰራዊት ከእጅህ አምልጦአል።
8 ኢትዮጵያውያንና ሊቢያውያን ብዙ ቊጥር ካላቸው ሠረገላዎቻቸውና ፈረሶቻቸው ጋር ኀያል ሰራዊት አልነበሩምን? ይሁን እንጂ በእግዚአብሔር ስለ ታመንህ በእጅህ አሳልፎ ሰጠህ፤