2 ዜና መዋዕል 18:24-30 NASV

24 ሚካያም፣ “ለመሸሸግ ወደ እልፍኝህ በምትሄድበት በዚያ ዕለት ታገኘዋለህ” አለው።

25 ከዚያም የእስራኤል ንጉሥ እንዲህ ሲል አዘዘ፤ “ሚካያን ይዛችሁ ወደ ከተማዪቱ ገዥ ወደ አሞንና ወደ ንጉሡ ልጅ ወደ ኢዮአስ መልሳችሁ ላኩት፤

26 እነርሱንም፣ ‘ንጉሡ፣ ይህን ሰው እስር ቤት አስገቡት፤ በደህና እስክመለስም ድረስ ከደረቅ ቂጣና ከውሃ በስተቀር ምንም አትስጡት ብሎአል’ በሏቸው።”

27 ሚካያም፣ “አንተ በደኅና ከተመለስክማ እግዚአብሔር በእኔ አልተናገረም ማለት ነው!” አለ፤ ቀጥሎም፣ “እናንተ ሰዎች ሁላችሁ ስሙኝ” አለ።

28 ስለዚህ የእስራኤል ንጉሥና የይሁዳ ንጉሥ ኢዮሣፍጥ ወደ ሬማት ገለዓድ ወጡ።

29 የእስራኤልም ንጉሥ ኢዮሣፍጥን፣ “እኔ ልብሴን ለውጬ ወደ ጦርነቱ እገባለሁ፤ አንተ ግን ልብሰ መንግሥትህን ልበስ” አለው። ስለዚህ የእስራኤል ንጉሥ ልብሱን ለውጦ ሌላ ሰው መስሎ ወደ ጦርነቱ ገባ።

30 በዚህ ጊዜ የሶርያ ንጉሥ የሠረገላ አዛዦቹን፣ “ከእስራኤል ንጉሥ በቀር፣ ትንሽም ሆነ ትልቅ ከሌላ ከማንም ጋር አትዋጉ” ብሎ አዘዛቸው።